በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር በወቅታዊ ሁኔታ የተነሳ በሜዳው ጨዋታውን ማካሄድ ያልቻለው ሀዋሳ ከተማ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በኢትዮጵያ ቡና 5-1 የሆነ አሰደንጋጭ ሽንፈትን አስተናግዷል። የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚም ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል፡፡
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች ለክለባቸው የቀድሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የምስጋና ስጦታ አበርክተዋል፡፡
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡናዎች ፍፁም የሆነ የጨዋታ የበላይነት የተስተዋለበት ነበር። የግብ ዕድሎችን በመፍጠር እንዲሁም በተሻለ የመከላከል አደረጃጀትና ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ፈጣን ሽግግሮች ለሀዋሳ ከተማ ፈተና ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡ በከተማው በነበረው አለመረጋጋት ልምምድ አቁመው የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች ይህንን በግልጽ በሚያሳይ መልኩ በጨዋታው በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በበርካታ መመዘኛዎች ሲታይ እጅግ ደካማ የሚባል ጨዋታን አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች የመጀመሪያውን አስደንጋጭ የሚባል የግብ ሙከራ ለማድረግ ሁለት ደቂቃዎች ነበር የፈጀባቸው። ሳሙኤል ሳኑሚ ከግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ግብ የላካትን ኳስ በዛሬው ጨዋታ በቅጣት ያልነበረው ሶሆሆ ሜንሳህን ተክቶ በመጀመሪያ ተሰላፊነት የሀዋሳን ግብ ሲጠብቅ የነበረው ተክለማርያም ሻንቆ በቀላሉ መያዝ ያልቻለውን ኳስ አስራት ቱንጆ ሞክሮ ወደ የግቡን ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ በግራ መስመር ባደላ መልኩ በሚደረጉ ሽግግሮች በተደጋጋሚ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል። ለዚህም ከሀዋሳ ከተማ አራት ተከላካዮች መካከል ወደ ፊት በመሄድ የሀዋሳን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማገዝ በማሰብ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳንኤል ደርቤ ወደ መከላከል በሚደረገው ሽግግር ወቅት ትቶ የሚሄደውን ክፍተት መልሶ ለመዝጋት መቸገሩ እንደዋነኛ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። ይህም በሀዋሳ የመሀል ተከላካይ የቀኙን ክፍል ላይ ጨዋታውን የጀመረውን መሣይ ጳውሎስን በተደጋጋሚ ወደ መስመር እየለጠጠ ሲጫወት ከነበረው የኢትዮጵያ ቡናው ብቸኛ አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ጋር በበርካታ አጋጣሚ 1ለ1 እንዲገናኝና የቡድኑን የመከላከል አደረጃጀት ተጋላጭ እንዲሆን በር ሲከፍት ተስተውሏል፡፡ በ18ኛው ደቂቃ ላይም የሀዋሳ ከተማው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ክሪዚስቶም ንታምቢ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳሙኤል ሳኑሚ በመምታት ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ይበልጥ ጫና በመፍጠር ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ27ኛው ደቂቃ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሰው ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላካት እና የሀዋሳ ተከላካዮች ተረባርበው ያዳኑበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡ ሀዋሳዎች የመጀመሪያዋን ግብ ካስተናገዱ በኃላ በደቂቃዎች ልዩነት በግራ መስመር ተከላካይነት የጀመረውና በርካታ ስህተቶችን ሲሰራ የነበረው ጌትነት ቶማስን አስወጥተው ወንድማገኝ ማዕረግን ወደ ሜዳ አስገብተዋል፡፡ በመጀመሪያ አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ክፍል በተደራጀ መልኩ ለመድረስ ሲቸገሩ የነበረ ቢሆንም በ34ኛው ደቂቃ በረጅሙ ከመሀል የተሻማውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ ኳሷን ለመያዝ በተነሳበት ቅፅበት ኳሷን ከያዘ በኃላ የሀዋሳ ከተማው የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነውን እስራኤል እሸቱን ተማቷል በሚል የእለቱ አርቢትር የሰጡትን የፍፁም ቅጣት ምት ፍሬው ሰለሞን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡
ለወትሮው በመሀል ሜዳ ላይ በርካታ ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ የሚታወቁት ሀዋሳ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ ይህ አጨዋወት በዋነኝነት የሚጠይቀው ትዕግስት ፍጹም አልነበራቸውም። በተቃራኒው በከፍተኛ ውዥንብር ውስጥ ሆነው በርካታ በቀላሉ ለቡድን አጋሮቻቸው ጋር መቀባበል የሚችሏቸው ኳሶች ሲባክኑባቸው ተስተውሏል። በ42ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ሳምሶን ጥላሁን ሲያሻማ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች የመለሱትን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረው ሳሙኤል ሳኑሚ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ ቡድኑን ዳግም ወደ መሪነት የመለሰች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከዚህች ግብ መቆጠር በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት መደበኛው 45 ተጠናቆ በተጨመሩ ደቂቃዎች ላይ መሳይ ጳውሎስ በእያሱ ታምሩ ላይ ጥፋት ሰርቷል በሚል የተሰጠውን አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ሳሙኤል ሳኑሚ ወደ ግብነት ቀይሮ ሐት-ትሪክ በመስራት የመጀመርያው አጋማሽ በቡና 3-1 መሪነት ተጠናቋል።
ጨዋታው ወደ እረፍት በሚያመራበት ወቅት የሀዋሳ ከተማ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትና ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ በከፍተኛ ሁኔታ ጨዋታውን የመሩት ዳኞች ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለሞዶ ካታንጋ እየባለ በሚጠራው የሜዳ ክፍል ላይ ለመቀመጫ የሚሆን ቦታ በማጣታቸው የተነሳ ከሜዳው በቅርብ ርቀት ይገኝ የነበረ ዛፍ ላይ ሆነው ጨዋታውን ሲከታተሉ የነበሩ የተወሰኑ ደጋፊዎች ዛፉ መገንደሱ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ከሁለተኛው አጋማሽ መጀመር አንስቶ በተሻለ ፍላጎት ሲጫወቱ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወትሮው በተለየ በዛሬው ጨዋታ እንደ ቡድን ተደራጅቶ በመከላከል እንዲሁም በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች በጣም የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡ ሀዋሳ ከተማዎችም ከመጀመሪያው በመጠኑም ቢሆን በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት ፍሬው ሰለሞን ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ጋብሬል አህመድ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ የላካትን የቡናው የመስመር ተከላካይ አስናቀ ሞገስ ከግቡ አፋፍ ላይ ለጥቂት አድኖበታል። ይህም ሐዋሳዎችን ወደ ጨዋታው ሊመልስ የሚችል ወሳኝ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከ60ኛው ደቂቃ አንስቶ የነበሩት አስር ደቂቃዎች በመጠኑም ቢሆን ተቀዛቅዞ የነበረው የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ ዳግም መነቃቃት አሳይቷል። በዚህም የኢትዮጵያ ቡናው አማካይ ሳምሶን ጥላሁን በ61ኛው ደቂቃ ከሀዋሳ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ኳሷን በግብ ጠባቂው አናት በማሳለፍ የቡድኑን መሪነት ወደ አራት ከፍ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ በሐዋሳዎች በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍቅረየሱስ ከቅጣት ምት የተሻማለትን ኳስ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እንዲሁም በፈጣን ሽግግር ኢትዮጵያ ቡናዎች ያገኟትን ኳስ ሚኪያስ መኮንን ሞክሮ ተክለማርያም ያዳነበት ተጠቃሽ የሁለተኛ አጋማሽ ሙከራዎች የተካሄዱት በነዚሁ 10 ደቂቃዎች ውስጥ ነበር፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ በጨዋታ ሂደት በተፈጠሩ ንኪኪዎች በኢትዮጵያ ቡና በኩል ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ እንዲሁም በሀዋሳዎች በኩል ደግሞ እስራኤል እሸቱ እና ሙሉአለም ረጋሳ በጉዳት ከሜዳ ለመውጣት ተገደዋል፡፡
በ93ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ያሳለፈለትን ኳስ ከሀዋሳው ግብ ጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ ሲመለስ የቀኝ መስመር ተከላካይ ኃይሌ እሸቱ በግሩም ሁኔታ አክርሮ መትቶ የማሳረጊያ ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና
“ምንም አይነት ስህተት መስራት በማይፈቀድልን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነን እንደመጫወታችን ተጫዋቾቼ ባሳዩት ነገር እጅግ በጣም ኮርቻለሁ።
ለዋንጫ የምንጫወት ከሆነ በቀጣይ ቀሪ ጨዋታዎች ላይ በዛሬው አይነት መልኩ መጫወት ይኖርብናል፡፡”
ውበቱ አበተ- ሀዋሳ ከተማ
“ለ11 ያክል ቀናት ልምምድ ሳንሰራ እንደመቆየታችን ጨዋታው ሊከብደን እንደሚችል እናውቅ ነበር። ተጋጣሚያችንን ውድድር ላይ እንደመቆየቱና ካላቸው ወቅታዊ አቋም የተነሳ ከሜዳችን ውጪ መጫወታችን ሰፊ ልዩነት አይፈጥርም፡፡ ነገርግን የጨዋታው ሚዛን ከእጃችን እንዲወጣ የተደረጉባቸው ሂደቶች ግን አሳማኝ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ለሽንፈታችን በምክንያትነት ባናቀርበውም ዳኝነቱ ፍትሃዊ ነው ብሎ ለመቀበል ከባድ ነው