የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፔን ጉዞ ተሰረዘ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ኤ.ኢ. ራማሳ ያቀረበለትን የወዳጅነት ጨዋታዎች ግብዣ መሰረዙን የክለቡ ልሳን በሆነው ‹‹ ልሳነ – ጊዮርጊስ ›› አስታውቋል፡፡ ፈረሰኞቹ ጉዞውን የሰረዙት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በሚያደርገው ዝግጅት ምክንያት ነው፡፡

ሁለቱ ክለቦች ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ አድርገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 6-0 ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን ከሳምንት በኋላ ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ካታሎን አቅንቶ ከኤ.ኢ. ራማሳ ጋር ጨዋታ ለማድረግ ታቅዶ ነበር፡፡ በስፔን ቆይታውም ከላሊጋው ክለብ ኤስፓኞል ሁለተኛ ቡድን ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ጨምሮ የኑ ካምፕ ስታዲየም ፣ ሙዝየሞች እና ባርሴሎና ከተማ ጉብኝት ፣ የልምድ ልውውጥ እና የመሳሰሉት በጉዞው የተካተቱ ነበሩ፡፡

በብራዚል በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ 11 ተጫዋቾችን ያስመረጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋናው ማጣርያ (ከአልጄርያ) ሊካሄድ ከወር ያነሰ ቀሪ ጊዜ በመቅረቱ እና ዋልያዎቹ በዝግጅት ተጠምደው የሚያሳልፉ በመሆናቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዞውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ከታላቅ ይቅርታ ጋር ለስፔኑ ክለብ በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን ክለቡም ደብዳቤውን ተቀብሎ በግንኙነታቸው እንደሚቀጥሉ ቃል መግባቱን ጋዜጣው ጨምሮ ገልጧል፡፡

ያጋሩ