የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 16ኛ ሳምንት አርብ ተካሂዶ በመሪዎቹ መካከል ያለው ልዩነት ወደ ቀጣዩ ሳምንት ሲሸጋገር ወራጅ ቡድኖች ሊታወቁም ተቃርበዋል።
ይርጋለም ላይ በዝናብ ምክንያት ከተያዘለት በአንድ ሰዓት ቀደም ብሎ የጀመረው የሲዳማ ቡናና ጌዲኦ ዲላ ጨዋታ በጌዴኦ ዲላ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ82ኛው ደቂቃ የእንግዶቹን ብቸኛ የድል ጎል ማስቆጠር የቻለችው የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ የሆነችው ሳራ ነብሶ ነች፡፡
ባንክ ሜዳ ላይ በተከናወነው ሌላው የ8 ሰዓት መርሐ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ መከላከያን 1-0 በመርታት ከመውረድ ስጋት የራቀበትን ውጤት አስመዝግቧል። የጎሉ ባለቤት ትመር ጠንክር ናት። መከላከያ በሁለተኛው ዙር መጥፎ ጉዞ እያደረገ ሲገኝ ከመሪው ደደቢትም በ13 ነጥቦች ለመራቅ ተገዷል።
ሀዋሳ ላይ ከነበረው የከተማዋ የፀጥታ ችግር በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና ኤሌክትሪክ መካከል ተካሂዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሙሉ የጨዋታ ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳዎች ከተደጋጋሚ እድሎች በኋላ በ32ኛው ደቂቃ ላይ በልደት ተሎዓ አማካኝነት ቀዳሚ መሆን ቢችሉም መሪነታቸው የዘለቀው ለአራት ደቂቃ ብቻ ነበር። በ36ኛው ደቂቃ ላይ ጤናዬ ወመሴ በግራ በኩል ሰብራ በመግባት በቀጥታ አክርራ መትታ የግብ ጠባቂዋ አባይነሽ ኤርቀሎ ስህተት ታክሎበት ግሩም ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪክን አቻ ማድረግ ችላለች። ከእረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት ያደረጉበት እና ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን የያዘበት ሆኖ ዘልቆ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት 1-1 ተጠናቋል።
ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለሜዳው ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ከመሪው ደደቢት ያለውን ርቀት አስጠብቆ ወጥቷል። በ18ኛው ደቂቃ ላይ ረሂማ ዘርጋ ባስቆጠረችው ግብ ባንክ 1-0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል ሊያመሩ የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ 45ኛው ደቂቃ ላይ ታዳጊዋ አጥቂ ነብያት ሀጎስ ድሬዳዋን አቻ ማድረግ ችላለች፡፡ ከእረፍት መልስ ደግሞ 61ኛ ደቂቃ ላይ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት አጥቂዋ ሽታዬ ሲሳይ በአግባቡ ተጠቅማ ጨዋታው በንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ባንክ ሜዳ ላይ አዳማ ከተማን የገጠመው ደደቢት 3-0 በማሸነፍ መሪነቱን አስጠብቋል። ሎዛ አበራ በ2ኛው እና 26ኛው ደቂቃ ባስቆጠረቻቸው ጎሎች ቡድኗ 2-0 እንዲመራ ከማስቻሏ በተጨማሪ የግብ ድምሯን 17 በማድረስ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ሰንጠረዥ ላይ መገስገሷን ቀጥላለች። የደደቢትን ሶስተኛ ጎል ያስቆጠረችው ሌላዋ አጥቂ ሰናይት ባሩዳ በ36ኛው ደቂቃ ነው።
ሊጠናቀቅ ሁለት ሳምንታት እድሜ ብቻገየቀረው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀራቸው ደደቢት እና ባንክ በ3 ነጥቦች ልዩነት በሰንጠረዡ አናት ላይ እየተፎካከሩ ይገኛሉ። በተለይም በቀጣዩ ሳምንት (17ኛ ሳምንት) እርስ በእርስ የሚገናኙበት መርሐ ግብር የዋንጫውን መዳረሻ የሚጠቁም ይሆናል።
ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመውረዱ ነገር እርግጥ የሆነ ይመስላል። ድሬዳዋ ቀሲ ሁለት መርሐ ግብሮቹን በሰፊ ልዩነቶች ተሽንፎ ኤሌክትሪክ በተቃራኒው ሁለቱንም ቀሪ መርሐ ግብር በሰፊ ልዩነቶች ካላሸነፈ በቀጣዩ ዓመት በ2ኛ ዲቪዝዮን የምንመለከተው ይሆናል። 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡናም የመትረፍ እድሉ በ3 ነጥቅ በሚርቀው ድሬዳዋ ከተማ ውጤት ላይ የተመሰረተ ነው።
የቀጣይ ሳምንት መርሐ ግብር
ሀዋሳ ከተማ ከ መከላከያ
ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና
ጌዴኦ ዲላ ከ ድሬዳዋ ከተማ
ኢት. ንግድ ባንክ ከ ደደቢት
አዳማ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የደረጃ ሰንጠረዥ
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች