በ2009 በቀድሞ የትራንስ ኢትዮጵያ አሰልጣኝ ም/ኮማንደር ዮሃንስ ሲሳይ የተመሰረተው ብሩህ ተስፋ አካዳሚ በሐምሌ ወር በስዊድን ጎተንበርግ በሚካሄደው አለም አቀፍ የታዳጊዎች ውድድር እንደሚሳተፍ ታውቋል። በሶስት የእድሜ እርከን የሚገኙ 100 ህፃናትን በማቀፍ እየሰራ የሚገኘው ይህ አካዳሚ በውድድሩ ላይ በሶስቱም የ እድሜ እርከኖች የሚወዳደርም ይሆናል።
በፈረንጆች አቆጣጠር ከ ጁላይ 15-21 የሚካሄደው ይህ ውድድር ከ80 ሀገራት የተወጣጡ 1700 ቡድኖች የሚሳተፉበት ትልቅ ውድድር ነው። በ1975 የተጀመረው ይህ ውድድር አለን ሽረር (ዊሊንግተን ጁንየርስ) ፣ አንድርያ ፒርሎ (ዬኤስ ቮለንታስ) ዣቪ ኣሎንሶ (አንቲጉኮ ) እና ዝላታን ኢቭራሂሞቪች የመሳሰሉ ታላላቅ ተጫዋቾች ተሳትፈውበት አልፈዋል።
ስለ ውድድሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኙ ዮሀንስ ውድድሩ የመጀመርያቸው እንደመሆኑ ብዙ ልምድ እንደሚያገኙበት እና ከሌሎች ሀገራት አካዳሚዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው በመግለፅ ጉዞው እንዲሳካ ትልቅ አስተዋፅኦ ላደረጉት የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና አቶ አስገዶም ተወልደ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ከዚ በተጨማሪ አካዳሚውን ለማስፋት ለቀጣይ አመት ምዝገባ ከሐምሌ 1 እስከ 3 በመቐለ ከተማ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም በ2007 በአልጣኝ አብርሀም ተ/ኃይማኖት እና አሰግድ ተስፋዬ ይመራ የነበረው ፓሽን አካዳሚ በውድድሩ ላይ መካፈሉ የሚታወስ ነው።