ሪፖርት | መከላከያ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ አዲስ አበባ ላይ መከላከያ መውረዱን ያረጋገጠው ወልዲያን አስተናግዶ ሁለት ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በቀዝቃዛማው የአዲስ አበባ ስታዲየም አየር በተከናወነው ጨዋታ የአንድ ቡድን የበላይነት የተስተዋለ ሲሆን በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ ባለሜዳዎቹ እጅግ ተሽለው ሲጫወቱ ታይቷል። መውረዱን ገና በጊዜ ያረጋገጠው እና በዛሬው ጨዋታ በተሻለ የአዕምሮ ነጻነት ወደሜዳ በመግባት የተሻለ ቡድን ያሳያል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ወልዲያ የአሰልጣኝ ስዩምን ስብስብ መፎካከር ሳይችል ቀርቷል።

9 ሰዓት በጀመረው ጨዋታ የጎል ሙከራዎች የተስናገዱት ገና በጊዜ ሲሆን ምንይሉ ወንድሙ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ ታኳ ወደ ውጪ የወጣችበት መከላከያን ቀዳሚ ልታደርግ የምትችል ጥሩ የግብ ማግባት እድል ነበረች። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ የመጀመሩያውን የጨዋታ ሙከራ ያደረገው ምንይሉ ከሳሙኤል ጋር አንድ ሁለት ተቀባብለው ወደ ወልዲያ የፍፁም ቅጣት ምት በመግባት የግብ ጠባቂው ቤሊንጌን አቋቋም በመመልከት የመታው ኳስ ከመረብ አርፎ የመከላከያን ገና በጊዜ መሪ ማድረግ ችሏል።

ጫናዎችን ማድረጋቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች አሁንም ቶሎ ቶሎ ወደ ወልዲያ የፍፁም ቅጣት ምት መድረስ የቻሉ ሲሆን በ22ኛው ደቂቃም ምንይሉ ለፍፁም ገ/ማርያም የሰጠውን ኳስ ፍፁም ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ወልዲያዎች በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ተዳክመው ቢታዩም አልፎ አልፎ በሚልኳቸው ረጃጅም ኳሶች ጎሎችን ለማግባት ሞክረዋል። በዚሁ የጨዋታ ሁኔታ በላይ አባይነህ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ኤደም በግንባሩ ገጭቶ አቤል ማሞ በሚገርም ብቃት ኳሷን አውጥቷታል።

ከአንድ ደቂቃ በኃላ ወልዲያዎች የሞከሩትን ኳስ መከላከያዎች በሚገባ ተቆጣጥረው በመልሶ ማጥቃት ወደ ወልዲያ የፍፁም ቅጣት ምት በሚገርም የማጥቃት ሽግግር ደርሰው ሳሙኤል ሳሊሶ ለፍፁም አቀብሎት ፍፁም በቀድሞ ክለቡ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ከጎሎች  መቆጠር በኃላ በትንሹም ቢሆን የመጫወት ፍላጎት የተስተዋለባቸው የወልዲያ ተጫዋቾች ተረጋግተው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም ምንም የግብ እድል ሳይፈጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽን አጠናቀዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በጣለው ዝናብ ምክንያት መከላከያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቅዘው ብለው የተጫወቱ ሲሆን ወልዲያዎች በተቃራኒው ለመነቃቃት ሞክረዋል። በ55ኛው ደቂቃ ወልዲያዎች በመስፍን ኪዳኔ አማካኝነት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ምንም እንኳም ጥቂት ቢሆኑም ያለቀላቸው የግብ እድሎችን ሲያመክን የነበረው አቤል በሚገባ ተቆጣጥሯታል። የሜዳው አለመመቸት እና የሚፈልጉትን ነገር በጊዜ በማግኘታቸው ምክንያት ጫናዎችን የቀነሱት መከላከያዎች በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ፍፁም ከታፈሰ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ቤሊንጌ አምክኗታል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙሉቀን አከለ ከመስፍን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ከባዶ ከመሸነፍ የሚያድናቸውን አጋጣሚ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ኳሷን ፊትለፊት በመምታቱ አቤል በሚገባ ተቆጣጥሯታል።

ጨዋታው በመከላከያ 2-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ጦሩ ነጥቡን 35 በማድረስ ከመውረድ ስጋት ሙሉ በሙሉ ቢይሆንም መውጣት ችሏል።