የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተካሂደው ጅማ አባጅፋር ድል ሲያስመዘግብ መቐለ ከተማ የዋንጫ ተስፋውን ያጨለመበት አዳማ ከተማ ከፉክክር የወጣበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በቅጣት ምክንያት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ጨዋታውን ያደረገው ጅማ አባጅፋር ደደቢትን አስተናግዶ 3-0 በማሸነፍ በዋንጫ ፉክክሩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንገት ለአንገት መተናነቁን ቀጥሏል።
ኦኪኪ አፎላቢ በ17ኛው ደቂቃ ከተመስገን ገብረኪዳን የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ ቀዳሚ አድርጓል። ጎሉ ከደደቢት በኩል ከጨዋታ ውጪ ነው የሚል ተቃውሞ ሲያስከትል የመስመር አጥቂው ኤፍሬም አሻሞ ከዳኛው ጋር በገባው እሰጥ እገባ ኢንተርናሽል ዳኛ በላይ ታደሰ የቀይ ካርድ ተመዞበታል። በ51ኛው ደቂቃ ተመስገን ገብረኪዳን ከኦኪኪ የተሻገለትን ኳስ ተጠቅሞ የደደቢትን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ሲያደርግ በ79ኛው ደቂቃ በደደቢት የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኦኪኪ አምክኖታል። ኦኪኪ በውድድር አመቱ የፍፁም ቅጣት ምት ሲያመክን ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ሆኖም በ90ኛው ደቂቃ ሳምሶን ቆልቻ ያመቻቸለትን ኳስ አስቆጥሮ ጅማ 3-0 እንዲያሸንፍ ረድቷል። የግብ መጠኑንም 19 አድርሶ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር ተቃርቧል።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር የሊጉ መሪነቱን ለሁለት ሰዓታት ይዞ ቢቀጥልም ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፉ በርካታ ጎል በማስቆጠር ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ዓዲግራት ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ወልዋሎ 1-0 በማሸነፍ ላለመውረድ የሚያደርገው ትግል ላይ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል። የወልዋሎን ወሳኝ የድል ጎል ያስቆጠረው ቡርኪና ፋሷዊው አጥቂ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ነው። በውጤቱ መሰረት አዳማ ከተማ ከመሪዎቹ በ8 ነጥቦች ርቆ ከቻምፒዮንነት ፉክክሩ መውጣቱን ሲያረጋግጥ ወልዋሎ ነጥቡን 34 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው በ5 ነጥብ መራቅ ችሏል።
በሀዋሳ አለምዓቀፍ ስታድየም ሊካሄድ ታስቦ በይርጋለም ስታዲየም የተካሄደው የሲዳማ ቡና እና መቐለ ከተማ ጨዋታ በባለሜዳው 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመርያ አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት መቀቐለ ከተማዎች ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ፉሴይኒ ኑሁ በ13ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 በመምራት የመጀመርያውን አጋማሽ አጠናቀዋል።
2ኛው አጋማሽ የሲዳማ ቡና ፍፁም የበላይነት የታየበት ሲሆን በ50ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ ሲዳማ ቡናን አቻ አድርጓል። በ75ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ አዲሱ ተስፋዬ ያሻገረውን ኳስ አዲስ ግደይ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ለቡድኑም ለራሱም ሁለተኛውንና የማሸነፈያ ግብ አስቆጥሯል። በ80ኛ ደቂቃ ሐብታሙ ተከስተ በአዲሱ ላይ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ውጠቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ35 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው ሲርቅ መቐለ ከተማ ከመሪዎቹ በ5 ነጥቦች ርቆ የዋንጫ ተስፋው ጨልሟል።