የ2018 የመላ አፍሪካ ዩኒቨርስቲ ጨዋታዎች በመቐለ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት በትላንትናው እለት በደማቅ የመክፈቻ ስነስርዓት ተጀመረ።
መስከረም 20 ቀን 2010 በዶ/ር ከሰስተ ለገሰ አማካኝነት የአዘጋጅነት ኃላፊነቱን የተቀበለው መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ ባለፉት ወራት ሰፊ ዝግጅት በማረግ ሁለት የእግር ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ አራት ሜዳዎችን በማዘጋጀት ለውድድሩ ዝግጁ መሆን ችሏል።
በ 1971 በጋና አክራ በአስር ተሳታፊ ሃገራት የተጀመረው ውድድሩ እንደ አንጋፋነቱ በተካሄደባቸው ሀገራት በቂ ትኩረት በሚድያ ሽፋን ሲሰጠው አይታይም። ይህ ውድድር ከ3 ዓመት በኋላ ግዜውን ጠብቆ በኬንያ ናይሮቢ ቢካሄድም ከዛ በኋላ በነበረው ኣመታት ባልታወቀ ምክንያት ሳይካሄድ ቆይቶ በ2004 በናይጄርያ ባውንቺ ድጋሚ መጀመር ችሏል። ብዙም ደማቅ ባልነበረው እና ዘጠኝ ተሳታፊ ሀገራት ብቻ ካሳተፈው ከጆሃንስበርጉ የ2016 ውድድር የተሳታፊ ሀገራት ቁጥርን በእጥፍ ጨምሮ የሚካሄደው የዝንድሮ ውድድር ከባለፋት አመታት በተሳታፊ ቁጥርም በሜዳ ጥራትም የተሻለ ውድድር እንደሚሆን ይገመታል።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ውድድር (Epusa) ፕሬዝዳንት አቶ ዓባይ ኪዳነን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት የተካሄደውና 5 ሰዓት የፈጀ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት በአትሌት ገ/እግዚዓብሄር ገ/ማርያም ውድድሩን መከፈቱን የሚያበስር ችቦ ተለኩሶ ተጠናቋል። ውድድሩ ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲጀምር እስከ ሰኔ 29 ድረስም የሚቆይ ይሆናል።