በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ደደቢት አርባምንጭን 2-1 በረታበት ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ላይ የተገቢነት ጥያቄ ያቀረበው አርባምንጭ ከተማ ክሱ ውድቅ ተደርጎበታል፡፡
አርባምንጭ ከተማ የደደቢቶቹ አቤል ያለው እና ሥዩም ተስፋዬ በ5 ቢጫ ካርድ ማረፍ ሲገባቸው በጨዋታው ተሳትፈዋል በሚል የተገቢነት ክስ ማቅረቡ ይታወቃል። ጉዳዩን ሲመረምር የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ጉዳዩን ሲያጣራ ቆይቶ አቤል ያለው 5 ቢጫ ካርድ እንዳልሞላ እና ሥዩም ተስፋዬ ደግሞ የነበረበት የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ ላይ ተግባራዊ በማድረጉ እና የቅጣት ክፍያውንም የከፈለ በመሆኑ ምክንያት አርባምንጭ ከተማ ያቀረበው የተገቢነት ክስ ውድቅ መደረጉን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ እና ከፌድሬሽን ያገኘችሁ መረጃ ያመለክታል፡፡
አርባምንጭ ከተማ በአሁኑ ወቅት 29 ነጥቦችን ሰብስቦ 15ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከመትረፊያ ደረጃው በሁለት ነጥቦች ርቋል።