ድሬዳዋ ከነማ 7 ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ብሄራዊ ሊጉን በድል አጠናቆ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ድሬዳዋ ከነማ ከግማሽ ደርዘን በላይ ተጫዋች በማስፈረም ቡድኑን እያጠናከረ ይገኛል፡፡ ቡድኑ የፕሪሚየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ከማስፈረሙ በተጨማሪ በብሄራዊ ሊጉ መልካም አቋም ያሳዩ ተጫዋቾችንም የግሉ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከላካይ የነበረው ተስፋዬ ዲባባ ድሬዳዋ ከነማ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ እና ኢትዮጵያ ቡና ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በንግድ ባንክ የመሰለፍ እድል ያላገኘ ሲሆን የኮንትራቱን ማለቅ ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ አምርቷል፡፡ ተከላካዩ በድሬዳዋ ከወንድሙ ወርቅነህ ዲባባ ጋር የመገናኘት እድል ፈጥሮለታል፡፡ የቀድሞው የሱሉልታ ከነማ ግብ ጠባቂ ወርቅነህ በድሬዳዋ ከነማ የብሄራዊ ሊጉ ጉዞ ብዙም ተሳትፎ ባያደርግም ድሬዳዋ በሩብ ፍፃሜው አዲስ አበባ ከነማን በመለያ ምት አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን እንዲቀላቀል 2 ኳሶችን በማዳን ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ግዙፉ ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ከ2 አመት በኋላ ወደ ምስራቅ ተመልሷል፡፡ የቀድሞው የአየር ኃይል ፣ ኤሌክትሪክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ በድጋሚ ቅዱስ ጊዮርጊስን በ2005 ከመቀላቀሉ በፊት ለሐረር ቢራ መጫወቱ የሚታወስ ነው፡፡ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ መድን የተጫወተ ሲሆን ለድሬዳዋ ከነማ ከመፈረሙ በፊት ለወላይታ ድቻ ለመፈረም በቃል ደረጃ ተስማምቶ ነበር ተብሏል፡፡ ወላይታ ድቻ ሳምሶንን ለማስፈረም በፌዴሬሽን በተገኘበት ወቅት ድሬዳዋ ከነማዎች የተሻለ ገንዘብ አቅርበውለት ለብርቱካናማዎቹ መፈረሙ ተነግሯል፡፡

የድሬዳዋ ከነማዋ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ግን የሚወራው ነገር መሰረተ ቢስ መሆኑን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ማንም ምንም ቢል እኛ ሳምሶንን ያስፈረምነው ገቢውን መንገድ ተጠቅመን ነው›› ብለዋል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ከፕሪሚየር ሊጉ በወረደው ወልድያ ቡድን ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ተከላካዩ ፍሬው ብርሃን ድሬዳዋ ከነማን የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ ሄኖክ አዱኛ ከ ሃላባ ከነማ ፣ የቀድሞው የወልድያ አጥቂ አቅሌስያ ግርማን ከ ወሎ ኮምቦልቻ እንዲሁም ዘላለምን ከደቡብ ፖሊስ አስፈርመዋል፡፡ ሲሳይ ደምሴም ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

ድሬዳዋ ከነማ በርካታ ተጫዋቾች ማስረሙን ተከትሎ አሰልጣኝ መሰረት ከቡድን ስብስቡ 9 ተጫዋቾችን ለመቀነስ ከውሳኔ ደርሰዋል፡፡ በክለቡ ከነበሩት 16 ተጫዋቾች ቀጣዩ የውድድር ዘመንን በድሬዳዋ የሚያሳልፉ ሲሆን የሚሰናበቱት 9 ተጫዋች ከክለቡ ሽልማት በኋላ የሚታወቁ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በተያያዘ ዜና ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል አስተያየት ሰጥቶ የነበረው የብሄራዊ ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ በላይ አባይነህ በክለቡ ለመቆየት ሳይስማማ እንዳልቀረ ከክለቡ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ያጋሩ