ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ወራጅ ቡድኖች ሲታወቁ ደደቢት የዋንጫ መንገዱን አሳምሯል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የአንደኛ ዲቪዝዮን 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደዋል። ከፍተኛ ትኩረት ያገኘው የንግድ ባንክ እና ደደቢት ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ከሊጉ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል። 

ባንክ ሜዳ ላይ በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋን ይዘው የተገናኙት ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ በኤሌክትሪክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመርያውን አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ኤሌክትሪኮች በዓለምነሽ ገረመው ግሩም ጎል በመሪነት ወደ እረፍት ሲያመሩ በ60ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ገረመው በድጋሚ ሁለተኛውን አክላ መሪነታቸውን አስፍተዋል። ሲዳማ ቡናዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው መመለስ ቢችሉም ዓይናለም ጸጋዬ ሶስተኛውን ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በኤሌክትሪክ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሆኖም ድሬዳዋ በዛሬው ጨዋታ አአቻ በመለያየቱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ መሻሻል ያሳየው ኤሌክትሪክ እና ሲዳማ ቡና ተያይዘው ወደ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ለመውረድ ተገደዋል።

በተመሳሳይ 08:00 ላይ የጀመረው የጌዲኦ ዲላ እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ጎል ሳይስተናግድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ሲዳማ ቡና በኤሌክትሪክ በመሸነፉ ምክንያትም ድሬዳዋ ከተማ ለከርሞ በሊጉ መሰንበቱን ማረጋገጥ ችሏል።

አዳማ ላይ በ09:00 አዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ሴናፍ ዋቁማ በ45ኛው እና 88ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግብ ስታስቆጥር ሌላውን አንድ ግብ አይዳ ዑስማን 87ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥራለች፡፡

ሀዋሳ ላይ አስቀድሞ ከ17 ዓመት በታች ተስተካካይ ጨዋታ በመኖሩ ምክንያት 10 ሰዓት ላይ በጀመረ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ መከላከያን 1-0  አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ የሀዋሳ ከተማዋ አጥቂ ልደት ቶሎአ ባንፀባረቀችበት ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ሀዋሳዎች በልደት እና ምርቃት ፈለቀ ተደጋጋሚ ሙከራን ሲያደርጉ መከላከያ በሄለን ሰይፉ እና ምስራች ላቀው አማካኝነት የግብ እድሎችን ቢያገኙም ግብ ሳይስተናገድ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ገና ሁለት ደቂቃ እንደተቆጠረ 47ኛው ደቂቃ ምርቃት በረጅሙ የላከችውን ኳስ ልደት ቶሎአ ተቆጣጥራ ሀዋሳን አሸናፊ ያደረገች ብቸኛ ግብ አስቆጥራለች፡፡ በ69ኛው ደቂቃ የሀዋሳዋ ግብ ጠባቂ ኳስ በእጅ በመያዝ ኳስ በማዘግየቷ በሳጥን ውስጥ የተገኘችውን የ2ኛ ቅጣት ምት ሔለን እሸቱ መትታ በግብ ጠባቂዋ ዓባይነሽ የተመለሰባት በመከላከያ በኩል አቻ ሊያደርግ የሚችል አጋጣሚ ነበር።

በ3 ነጥብ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት የሚገኙት ደደቢት እና ንግድ ባንክን ያገናኘው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የባንክ ሜዳ በዝናብ ምክንያት ለጨዋታ አመቺ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከጨዋታው መጀመር በፊት በሁለቱ ቡድን አባላት መካከል የተነሳ ፀብ ጨዋታው ውጥረት የነገሰበት እንዲሆንበት አድርጎታል። በሁለቱም አጋማሽ የጠራ የጎል ሙከራ ያልተሰናገደበት ይህ ጨዋታ ላይ ደደቢቶች በአጭር ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለማምራት ያደረጉት ጥረት በመሐለኛው የሜዳ ክፍል መጨቅየት ምክንያት በተደጋጋሚ ሲቆራረጥ ታይቷል። በንግድ ባንክ በኩል ደግሞ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በረጃጅም ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ደደቢት ከተከታዩ ንግድ ባንክ ያለውን የ3 ነጥብ ርቀት አስጠብቆ በመውጣት ለአራተኛ ተከታታይ ዓመት የሊጉ ቻምፒዮን ለመሆን ተቃርቧል።

ፕሪምየር ሊጉ ሊጠናቀቅ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች እና የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ ይቀራሉ።

የደረጃ ሰንጠረዥ

ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች