የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ፊፋ በ2018 የዓለም ዋንጫ መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ እንዲታደሙ ያቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው ረቡዕ ጠዋት ወደ ሞስኮ አቅንተዋል፡፡
ፊፋ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜው ላይ እንዲታደሙ የሃገራት እግርኳስ ማህበራት እና ፌደሬሽኖች ፕሬዝደንቶችን የጋበዘ ሲሆን ይህንን ጥሪ በመቀበል ነው አቶ ኢሳይያስ ወደ ሞስኮ ያመሩት፡፡ አቶ ኢሳይያስ በያዝነው ሰኔ ወር መጀመሪያ ወደ ሩሲያ አቅንተው የፊፋ ኮንግረስ እና የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ መታደም ችለዋል፡፡ በፊፋ ኮንግረሱ ወቅት ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት ፌዴሬሽን ላልተሳካው የሞሮኮ የ2026 የዓለም ዋንጫ አዘጋጅነት ጥያቄ ድጋፍ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
አፍሪካን የወከሉት አምስቱ ሃገራት (ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል እና ቱነዚያ) በሙሉ ከ1982 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከምድብ ማለፍ ተስኗቸው በጊዜ ወደ መጡበት ተሸኝተዋል፡፡ በብዙ መመዘኛዎችም የዓለም ዋንጫው ለአምስቱ የአህጉሪቱ ብሔራዊ ቡድኖች ደካማ ማለት ነበር ይቻላል፡፡
ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት እድሜ በቀረው የዓለም ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ በመጪው አርብ ዩራጓይ እና ፈረንሳይ በሚያደርጉት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ይቀጥላል።