በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በደረጃ ሰንጠረዡ በ35 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ወጣ ገባ አቋም እያሳየ ይገኛል። ዘንድሮም እንደ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ሁሉ አመቱ ሲጀመር የተጨዋቾች ግዢን የፈፀመው ሀዋሳ ባሰበው መንገድ መጓዝ ሳይችል ቀርቷል። ከእነዚህ ተጨዋቾች መሀከል ከሁለት አመት በኃላ ዳግም ወደ እግር ኳስ ተመልሶ ለአንድ አመት ያህል ፊርማውን ያኖረው ሙሉዓለም ረጋሳ አንዱ ነው። ተጨዋቹ በክለቡ በአማካይ ስፍራ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ በተለይ ሀዋሳ ላይ በሚደተጉ ጨዋታዎች ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ ቆይቷል።
ከዚህም ባለፈ ቡድኑ ጅማ አባ ጅፋርን እና ድሬዳዋ ከተማን በረታበታባቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ያስገኙ ግቦችን ማስቆጠሩ ይታወሳል። ይሁን እና ‘ተጫዋቾቹ ያለ ክለቡ ፈቃድ ወደ አሜሪካ በማቅናቱ ‘ በሚል እና በኢትዮጵያ ቡና ከተረቱበት ጨዋታ በኃላ ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ባለመግባባቱ ከክለቡ ጋር በውሉ ማብቂያ ጊዜ ተለያይቷል። ሙሉአለም በቀጣይ ሀዋሳ ከተማ ወልዋሎ ዓ.ዩን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚገጥምበት ጨዋታ ላይም የማይሳተፍ ይሆናል፡፡
ሌላኛው ክለቡን የለቀቀው ኮትዲቫራዊው የመሀል ተከላካይ ሲይላ መሀመድ ነው። ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ክለቡን ለ 6 ወራት ያክል ተቀላቅሎ ዘንድሮም አብሮ የቀጠለው የመሀል ተከላካዩ ከሲዳማ ቡናው የ26ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ ተጫዋቹ ደካማ አቋም እያሳየ በመሆኑ አንዲሁም የመኖሪያ ፍቃዱ በመጠናቀቁ ከሰኔ 10 ጀምሮ ደግሞ ወደ ሀገሩ አቅንቷል።
ሀዋሳ ከተማ በቀጣዩ አመት ወደ ቀደመ ተፎካካሪነቱ ለመመለስ በርካታ የተጫዋች ግዢ እና አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ እንዳሰበ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ ተጨማሪ መረጃ ይጠቁማል፡፡