ከሰኔ 24 ጀምሮ በመቐለ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የመላው አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር በትላንትናው እለት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ከ18 ሀገራት የተውጣጡ 56 ዩኒቨርሲቲዎች በ7 የውድድር አይነቶች በተካፈሉበት በዚህ ውድድር 37 ዩኒቨርሲቲዎች በሜዳልያ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። የዩጋንዳው ንዴጄ ዩኒቨርሲቲ 19 አጠቃላይ ሜዳልያዎች ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ የደቡብ አፍሪካው ጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ 12 ሜዳልያዎች 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 24 ሜዳልያዎችን መሰብሰብ ቢችልም በጆሀንስበርግ በአንድ የወርቅ ሜዳልያ በመበለጡ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። አዘጋጁ መቐለ ዩኒቨርሲቲ 6ኛ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ 13ኛ፣ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ 21ኛ፣ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ 24ኛ፣ ትክኒክ እና ሙያ ኮለጅ 31ኛ፣ አክሱም ዩኒቨርሲቲ 36ኛ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ 37ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የሜዳልያ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። በሀገራት ደረጃ ዩጋንዳ ቀዳሚ ስትሆን ኢትዮጵያ እና ጋና ተከታዩን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ከስፖርታዊ ውድድር ባለፈ የአፍሪካ ሃገራትን የወንድማማችነት ስሜት ለማጠናከር ያግዛል የተባለው ይህ ውድድር የባህል እና ልምድ ልውውጥ መድረኮችን ያካተተ ነበር። የመዝግያ ስነ-ስርዓቱ ትላንት ሲከናወንም የችግኝ ተከላ እና የሃውልት ምረቃን አጠቃሏል።