በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ወልዋሎን አስተናግዶ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
ከሰሞኑ ሀዋሳ ላይ ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጨዋታው በዝግ ስታዲየም ይደረጋል ተብሎ ቢወሰንም ከጨዋታው አስቀድሞ ግን ጥቂት ብቻ ደጋፊዎች መግባት አለባቸው በማለት የተወሰኑ ተመልካቾች ጨዋታውን እንዲከታተሉ ተደርጓል። የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለማሟሟቅ ዘግይተው ወደ ሜዳ በመግባታቸው ምክንያት ከሌሎች ጨዋታዎች 21 ያህል ደቂቃን ዘግይቶ የተጀመረው ጨዋታው የባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች የበላይነት ታይቶበታል። በ11ኛው ደቂቃ ጋብሬል አህመድ በግሩም ሁኔታ የሰጠውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከዮሀንስ ሽኩር ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሀዋሳን ቀዳሚ የምታደርግ አጋጣሚ መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በደስታ ዮሀንስ አማካይነት እድል አግኝተው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በ25ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሀንስ ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ እስራኤል እሸቱ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ስትወጣበት በ36ኛው ደቂቃ ከርቀት ጋብሬል አህመድ አክርሮ መትቶ ዮሀንስ እንደምንም አውጥቶበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ አብዱልከሪም ሀሰን ሀዋሳን መሪ የምታደርግ አጋጣሚን አግኝቶ ዮሀንስ ሽኩር መልሶበታል፡፡ በወልዋሎ በኩል በ30ኛው ደቂቃ ከእንየሁ ካሳሁን የተሻገረውን ኳስ አጥቂው ሪችሞንድ አዶንጎ በግንባሩ ገጭቶ የወጣችበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
ሁለተኛው አጋማሽ አሁንም በሀዋሳ ከተማ የበላይነት ሲቀጥል ወልዋሎዎች አቻ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ጥብቅ መከላከል ላይ አተኩረው ገብተዋል፡፡ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ጋብሬል አህመድ ወደ ግብ ሲመታ የላይኛውን የግቡን ቋሚ ብረት ታኮ የወጣበት በሀዋሳ በኩል ሲጠቀስ 60ኛው ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ፉይሴኒ የሰጠውን ኳስ ሪችሞድ መጠቀም ያልቻለበት ደግሞ በወልዋሎ በኩል ተጠቃሽ ነበር።
79ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎ አማካይ ዋለልኝ ገብሬ ዳዊት ፍቃዱ ሊያልፈው ሲሞክር በእጅ በመንካቱ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የመጨረሻወቹን 5 ደቂቃወች ሀዋሳ ከቅጣት ምት በፍሬው ሰለሞን እንዲሁም በዳዊት ፍቃዱ ደግሞ ሌላ አጋጣሚን ቢያገኙም ዩሀንስ ሽኩር አውጥቶባቸዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ብልጫን ይዞ ቢጫወትም በጥብቅ መከላከል ላይ ያተኮሩት ወልዋሎ ተሳክቶላቸው ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል። በውጤቱ ሀዋሳ ከተማ ቆይታውን ሲያረጋግጥ ወልዋሎም ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ በቀጣይ አመት በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል፡፡