በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ጎንደር ላይ በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ 1-0 አሸንፏል።
ፋሲሎች በ28ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በኤሌክትሪክ 4-1 አስተናግዶ 4-1 ከተሸነፈው ስብስብ በሰንደይ ምትኩ ምትክ ከቅጣት የተመለሰው ያሬድ ባየን ሲያሰልፍ ሄኖክ ገምቴሳን በናትናኤል አወቀ፣ ኤርሚያስ ኃይሉን ደግሞ በአብዱራህማን ሙባረክ ተክተው በ4-4-2 አሰላለፍ ነበር የገቡት።
በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከድሬደዋ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ ሀሪሰን ሄሱን በወንድወሰን አሸናፊ፣ ሚኪያስ መኮንንን በባፕቲስቴ ፋዬ፣ ኃይሌ ገ/ተንሳይን በትዕግስቱ አበራ፣ ሳምሳን ጥላሁንን መስዑድ መሀመድ እንዲሁም አማኑኤል ዮሀንስን በአክሊሉ ዋለልኝ ተክተው በ4-2-3-1 ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ለውጥ ነበር ወደ ጨዋታ የገቡት።
በቀላል ካፊያ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በወቅታዊው የአየር ሁኔታ ምክንያት የመጫወቻ ሜዳው አስቸጋሪ ሆኖ ኳስ ለማንሸራሸር አመቺ አልነበረም። የመጀመሪያውን 10 ደቂቃ የተሻለ ተጭነው መጫወት የቻሉት አፄዎቹ ገና በ6ኛ ደቂቃ ነበር ግብ ማግኘት የቻሉት። ሀሚስ ኪዛ ከግራ መስመር የመጀመርያ ጨዋታውን ካደረገው ናትናኤል ወርቁ የተሻማለትን ኳስ በጭንቅላቱ ገጭቶ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።
ከግቡ በኋላ አሰላለፋቸውን ወደ 4-2-3-1 የለወጡት ፋሲሎች ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ አድርገዋል። በሙከራ ደረጃ በ13ኛ ደቂቃ ላይ ከሰይድ ሀሰን የተሻማውን ኳስ ራምኬል ሎክ በጭንቅላት ቢገጭም ግብ ጠባቂ ወንደሰን አሸናፊ በግሩም ሁኔታ አድኖታል። በ 33ኛ ደቂቃ ላይ አብድራህማን ሙባረክ ወደ ግብ የመታው ኳስ በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ተነካክቶ በግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘበት የሚጠቀሱ ናቸው። በየመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ላይ ያለመረጋጋት የታየባቸው ቡናዎች በረጅም ኳሶች እድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በ14ኛው ደቂቃ ትዕግስቱ አበራ ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ሳማኪ በቀላሉ ሲያድንበት 31ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ክሪዚስቶም ንታንቢ በጥሩ ሁኔታ ቢመታውም ግብጠባቂ አውጥቶበታል። በ37ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ቱንጆ ከርቀት ወደግብ የመታው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ ታኮ የወጣውም በመጀመሪያው አጋማሽ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነው።
በጨዋታው አጋማሽ የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች መልካም 42ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ባነር አሰርተው ጥላፎቅ ላይ ለነበሩ ደጋፊዎች በማበርከት ለተወሰኑ ደቂቃዎች አብረው በመጨፈር ነበር የእረፍቱን ሰዓት ያሳለፉት።
ሁለተኛው አጋማሽ የአየር ሁኔታው ወደ ፀሀያማነት ሲቀየር ኢትዮጵያ ቡና ተጭኖ በመጫወት ጎሎችን ለማግኝት ጥረት አድርጓል። ፋሲሎች በበኩላቸው በጨዋታው ለጎል የሚሆን ኳስ አመቻችቶ ያቀበለው ናትናኤል አወቀን በሰንይ ሙቱኩ ተክተው የተከላካይ ቁጥር በማብዛት ይበልጥ አፈግፍገው በመልሶ ማጥቃት ለቡና አስቸጋሪ ሆነው ታይተዋል። በሙከራ በታጀበው ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከምቹ ቦታዎች ቅጣት ምት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ51ኛ ደቂቃ ላይ ክሪዚስቶም ንታንቢ መትቶ ሚኬል ሳማኬ ያወጣበት ሙከራም ለዚህ ማሳያ ነበር። 61ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከግራ መስመር አክርሮ የመታውን ግብጠባቂ ያዳነበት እንዲሁም 64ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ከሳኑሚ የተሻማን ኳስ ባፕቴስት ፋዬ ቢገጨውም ኢላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ፤ 79ኛ እና 81ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ሳምሶን ጥላሁን ከርቀት ሞክሮ በተመሳሳይ ኢላማቸውን ስተው የወጡበት እንዲሁም ከግራ መስመር በተጨማሪ ሰዓት ላይ ሳኑሚ የመታውን ኳስ በጨዋታዉ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው የፋሲል ከተማ ግብ ጠባቂ ሚኬል ሳማኪ በቀላሉ አውጥቶበታል።
በፋሲል ከተማ በኩል 65ኛ ደቂቃ ላይ ከራምኬል ሎክ የተሻገረለትን ኳስ ሀሚስ ኪዛ ሳይጠቀምበት ሲቀር 71ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ከርቀት ሰንደይ ምትኩ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት ቅጣት ምት እና ሀሚስ ኪዛ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ እንደገና በመልሶ ማጥቃት 73ኛ ላይ ሀሚስ ኪዛ ከገረብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረዉ በፋሲል በኩል የሁለተኛው አጋማሽ የሚያሰቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ።
ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደግብ መድረስ ቢችሉም ግብ ማስቆጣር አልቻሉም። በዚህም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ግብ በፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱ መሰረት ፋሲል ከተማ በ41 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ጭላንጭል የዋንጫ ተስፋ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ በ47 ነጥቦች ወደ 4ኛ ወርዷል።