በሊጉ 29ኛ ሳምንት መርሀ ግብር መቐለ ከተማ በጋቶች ፓኖም የዘገየች ብቸኛ ጎል ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፏል።
በሜዳቸው የአመቱን የመጨረሻ ጨዋታ ያደረጉት መቐለ ከተማዎች በጨዋታው ተሽለው ሲንቀሳቀሱ በተቃራኒው እንግዶቹ ኤሌክትሪኮች ብዙውን የጨዋታ ክፍለ ግዜ በራሳቸው ሜዳ በመገደብ ተደራጅተው ተከላክለዋል። ጨዋታው ተጀምሮ ደቂቃዎች ካስቆጠረ በኋላ ኤሌክትሪኮች የማልያው ቀለም ስለተመሳሰለ መቀየር አለበት የሚል ጥያቄ አንስተው ጨዋታው ለ 3 ደቂቃ ቢቋረጥም ዋና ዳኛው ጥያቄውን ሳይቀበሉ ጨዋታው መቀጥሏል።
መቐለ ከተማዎች በተለመደው 4-2-3-1 አሰላለፋቸው ጨዋታውን ሲጀምሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው 3-5-2 አጨዋወትን ይዘው ገብተዋል። በኤሌክትሪኮች በኩል የተሰለፉት መስመር ተመላላሾች (wing backs) ዓወት እና ዘካርያስ በማጥቃቱ እና በመካላከሉ በነበራቸው ሚዛናዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ቡድኑ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለ ግዜ በ 5 ተከላካዮችን ቢጠቀምም መቐለዎች በ ሁለቱም መስመሮች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተከላካዮች የመከላከል ቅርፅ ሚያስቱበት አጨዋወት ሙሉ በሙሉ መግታት ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመር ተጨዋቾች ወደ ራሳቸው ሳጥን እጅግ ቀርበው መጫወታቸው እና በጎሉ አከባቢ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን በንቃት ከመሸፈናቸው ሌላ በመቐለ የአጥቂ መስመር ላይ የቁጥር ብልጫ አስገኝቶላቸዋል። መቐለ ከተማዎች ሁለቱን የመስመር ተከላካዮች ሙሉ በሙሉ በማጥቃቱ ላይ እንዲሳተፋ በማረግ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች የጎል ዕድሎች መፍጠር ችልዋል። በተለይም ዳዊት ዑቁበዝጊ በማጥቃት እና በመከላከሉ ረገድ የነበረው ሚዛናዊነት የሚደነቅ ነበር።
ምንም እንኳን በ3ኛው የሜዳ ክፍል የነበረው ስኬታማነት ጥሩ ባይሆንም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመከላከሉ ላይ ቢጠመዱም በአልሃሰን ካሉሻ እና በኃይሌ እሸቱ የጎል ዕድል ፈጥረው ነበር። በተለይም ኃይሌ መቶት ለትንሽ ወደ ላይ የወጣበት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በጨዋታው እጅግ አናሳ የጎል ዕድል ቢፈጠሩም ባለሜዳዎቹ ከ ኤሌክትሪክ የተሻለ የጎል እድል መፍጠር ችለዋል በተለይም ፋሴኒ ኑሁ ከ ጋቶች ፖኖም በግሩም ሁኔታ የተላከችለትን ክዋስ ተጥቅሞ የመታት እና ተከላካዬች ተደርበው ያወጡበት እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሚካኤል ደስታ ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ጋናዊው ፉሰይኒ ሲሞክር ወደ ላይ የወጣው እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በረጅሙ የተላከችለት ኳስ ተጠቅሞ ግብ ጠባቂውን ኣታሎ ኣልፎ ሞክሮ ተከላካዮች ተረባርበው በህብረት ያወጡት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
በሁለተኛው አጋማሽ የኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ስዐት ለማባከን በሚወስዱት ዘለግ ያለ ደቂቃ እና መቐለዎች በማጥቃት ወረዳ ላይ በሚያሳዩት ህፀፅ የታጀበ ሆኖ ሲቀጥል ብዙ የጎል ዕድሎችም ያልታዬበት ነበር። ያሬድ ብርሃኑን በእያሱ ተስፋዬ ቀይረው ያስገቡት ባለሜዳዎቹ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ የተለጠጠ የተጫዋቾች ቦታ አያያዝ ይዘው ሲገቡ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመርያው ኣጋማሽ ምንም ኣይነት ለውጥ ሳያረጉ ነገር ህን የተሻሉ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። ኃይሌ እሸቱ በሁለት አጋጣሚዎች የፈጠራቸው የጎል ዕድሎች ተጠቃሽ ነበሩ። በተለይም ከማዕዘን የተሻገረለት እና በግንባር ገጭቶት ኢቮኖ እንደምንም ያዳነው እንዲሁም ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶት ኣሁንም ኦቮኖ ያዳነበት ኤሌክትሬክን መሪ ለማረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ።
መቐለዎች በአምስት ተከላካዮች እና በሁለት ለተከላካይ መስመሩ ቀርበው በሚጫወቱ አማካዮች የተደራጀው የኤሌክትሬክ ክፍተት ማይሰጥ የኃላ ክፍል ማስከፈት ሲቸግራቸው የታየ ሲሆን በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ መስመር ወጥቶ እንዲጫወት የተደረገው ፋሰይኒ ወደ ጎን ተጠግቶ ከመጫወት ይልቅ ብዙ የኤሌክትሪክ ተጨዋቾች ክምችት ወዳለበት ቦታ አጋድሎ ሲጫወት እና በቀላሉ በተከላካዮች እጅ ሲወድቅ የነበረ ሲሆን የተጨዋቹ የመጨረሻ ውሳኔ አሰጣጥም ጥሩ የሚባል አልነበም። በዚም ምክንያት የመቐለ የማጥቃት አጨዋወት በረጅሙ የሚጣሉ ኳሶች ላይ የተመረኮዘ ነበር። በረጃጅም ኳሶች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መቐለ ከተማዎች የጎል ዕድሎችም ፈጥረው ነበር። አንተነህ ገ/ክርስቶስ ነፃ አቋቋም ለነበረው ያሬድ ብርሃኑ በረጅሙ ያሻማት እና ያሬድ ሳይጠቀምባት የቀረችው እና አሞስ ኣቻምፖንግ በረጅሙ መቷት ለጥቂት የወጣችው ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ።
አጥቅተው የሚጫወቱት መቐለዎች ትተውት በሚሄዱት ክፍተት ኤሌክትሪኮች ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ቢፈጥርላቸውም በነበራቸው ደካማ የማጥቃት ፍላጎት ምክንያት መጠቀም ሳይችሉ ለብዙ ደቂቃዎች ቢቆዩም መጨረሻ ላይ ጥቂት የጎል ዕድሎች ፈጥረው ነበር። የዲዲዬ ለብሪ እና አልሀሰን ካሉሻ እነዚህ ሙከራዎች ግን በኢቮኖ ተመልሰዋል። መቐለ ከተማዎች ተከላካዩ ዳዊት እቁባዝጊን አስወጥተው አሸናፊ ሃፍቱን ሲያስገቡ የተከላካይ ቁጥራቸውን በመቀነስ በሶስት ተከላካይ መጫወት ከጀመሩ በኃላ በመሃል ሜዳ በቁጥር በዝተው ለብቸኛው አጥቂ አማኑኤል ቀርበው መጫወት መቻላቸውን ተከትሎ በርከት ያሉ የጎል ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። ያሬድ ብርሃኑ በረጅሙ መቶት ሱሌማን አቡ ያዳነበት ፣ ፋሰይኒ ከአንተነህ የተቀበለው እና አክርሮ መቶት ግርማ በቀለ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያወጣበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። በመጨረሻም በ90ኛው ደቂቃ ላይ ጋቶች ፖኖም ከሳጥን ውጪ ያገኘውን ኳስ አክርሮ መቶ መቐለን አሸናፊ አድርጓል። ኤሌክትሪኮች ከዛ በኃላ ተቀይሮ የገባውን ታፈሰ ተስፋየን በጫላ ድሪባ ቀይረው በማስወጣት የ አቻነት ጎል ፍለጋ ቢያጠቁም ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሣህሌ – መቐለ ከተማ
ጨዋታው ትንሽ ከበድ ይል ነበር ፤ እነሱ ዘግተው ስለ ተጫወቱ። መጨረሻ ላይ ግን የአጨዋወት ስልታችንን ቀይረን አንድ ጎል አግብተን አሸንፈናል።
በሜዳችን የመጨረሻው ጨዋታ ስለሆነ ታግለናል። በመጨረሻም ተሳክቶልን ደጋፍያችንን ማስደሰት ችለናል። ከልብ ከልብ ነው ደጋፍያችን የምናመሰግነው።