የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ለመሆን አምስት አሰልጣኞች በእጩነት ቀርበዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በሰራነው ዜና የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆኖ ለመቀጠር አስቀድሞ የወጣው የቅጥር መስፈት አጥጋቢ ባለመሆኑ ለመወዳደር ማመልከቻ ያስገቡት ጥቂት እንደሆነ ገልፀን ፌዴሬሽኑ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በመስፈርቱ ዙርያ ጥያቄዎች ማስነሳቱ እንዲሁም የማሰልጠን ፍላጎቱ የቀዘቀዘው ፌደሬሽኑ ያወጣው መስፈርት ለብዙ አሰልጣኞች ለመወዳደር አመቺ አለመሆኑን በቀሪዎቹ ቀናት ማመልከቻ የሚያስገቡት አሰልጣኞች ቀድመው ካስገቡት የተለየ ነገር ከሌለው ፌዴሬሽኑ አወዳድሮ ለመቅጠር የሚቸገር በመሆኑ ለተጨማሪ ቀናት ሊያራዝም እንደሚችል አልያም ሌላ መንገድ ሊከተል እንደሚችል መግለፃችን ይታወሳል።
አሁን በደረሰን ዜና መሠረትም ፌዴሬሽኑ የአሰልጣኝ ቅጥር መስፈርቱን በማስቀረት የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ኮሚቴ አምስት አሰልጣኞችን ለይቶ በመምረጥ ከዛሬ ጀምሮ በተናጥል በመጥራት ቃለ መጠይቅ ማድረግ ጀምረዋል። አምስቱ አሰልጣኞች የጅማ አባጅፋሩ አሰልጣኝ ገብረ መድህን ኃይሌ ፣ የወልዋሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ፣ የመከላከያ ሥዩም ከበደ ፣ የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የየመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ናቸው። ዛሬ በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በመገኘት ሦስተረ አሰልጣኞች (ገብረመድህን ፣ ሥዩም እና ፀጋዬ) ቃለ መጠይቅ የተደረጉ ሲሆን የቀሩት በነገው እለት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ቴክኒክ ኮሚቴው የአሰልጣኞቹን ቃለ መጠይቅ ካጠናቀቀ በኋላ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሂደቱን በማቅረብ በቅርብ ቀናት በይፋ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የአሰልጣኙ ቅጥር ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።