የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ አስመራ ላይ የወዳጅነት ጨዋታን ለማድረግ የኤርትራ ብሄራዊ እግርኳስ ፌደሬሽንን በድብዳቤ ዛሬ ጠይቋል፡፡
አጼዎቹ በድብዳቤያቸው የጎንደር እና የኤርትራን ታሪካዊ ትስስር ያወሱ ሲሆን የወዳጅነት ጨዋታው አስመራ ላይ ከአንድ የኤርትራ ክለብ ጋር ለማድረግ ነው ጥያቄያቸውን ለኤርትራ ፌደሬሽን የላኩት፡፡ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ አስመራ ባሳለፍነው እሁድ ያደረጉትን ታሪካዊ ጉዞ ጋር ተያይዞ ነው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄ ከፋሲል ከነማ ሊነሳ የቻለው፡፡
በ1990 በነሳው የድንበር ግጭት ተከትሎ በተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ ከኤርትራ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገው አያውቅም፡፡ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በሳምንቱ መጨረሻ ዳግም እንደሚጀመር የተበሰረ መሆኑን ተከትሎ በእግርኳስ ሜዳም ጨዋታዎች በሁለቱ ሃገራት ቡድኖች ከረጅም አመታት በኃላ መደረግ እንደሚጀምሩ ይታመናል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በ2014 የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) አንደኛ ዙር ላይ ተገናኝተው የነበረ ቢሆንም ኤርትራ ከጨዋታው ራሷን አግልላለች፡፡ በ2009 ኤርትራ ላይ በተደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ሳትሳተፍ ቀርታለች፡፡ በ2015 ኢትዮጵያ ላይ በተደረገው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ላይም ኤርትራ ተካፋይ አለመሆኗ የቅርብ ትዝታ ነው፡፡
በፋሲል ከነማ በኩል የተነሳውን የወዳጅነት ጨዋታ ጥያቄ ላይ በቀድሞ ኢንተርናሽናል አርቢትር ተስፋዬ ገብረየሱስ የሚመራው የኤርትራ ብሄራዊ እግርኳስ ፌድሬሽን መልስ የሚጠበቅ ይሆናል፡፡
ሙሉ ደብዳቤ