ፊፋ በምስራቅ አፍሪካ ያለው የእግርኳስ እንቅስቃሴን ለመከታተል ይከፍተዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን ቢሮ ኪራይ ውል መፈፀም ችሏል።
በጃንዋሪ ወር የፊፋ ተወካዮች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ እና ለቢሮ የሚሆኑ ህንፃዎችን በመመልከት መመለሳቸው የሚታወስ ሲሆን የቢሮው ኪራይ ጉዳይ ተጓትቶ ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት ፌዴሬሽኑ በጠራው ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንቱ አቶ ኢሳይያስ ጂራ እንደገለፁት ፊፋ ከመንግስት በኩል ያለውን ተነሳሽነት መመልከት እንደሚፈልግ በመግለፁ እንደተጓተተ ተናግረው የመንግስትን ምላሽ እንደሚጠባበቁ መናገራቸው ይታወሳል። የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴርም ለቢሮው መከፈት ትብብር እንደሚያደርግ መግለፁን ተከትሎ ፊፋ ቢሮውን ለመክፈት መወሰኑ ታውቋል።
ፊፋ አዲሱ ቢሮ ከፍሬንድሺፕ ሞል ጀርባ የሚገኝ ሲሆን 5 ክፍሎች እንዳሉትና ለ2 ዓመት በሚቆይ ውል እንደተከራየ ተገልጿል። ከሰኞ ጀምሮም የቢሮ ቁሳቁሶች እና ፊፋ የሚልካቸው ሰራተኞች ተሟልተውለት ስራውን የሚጀምር ይሆናል።