የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ ባገኘው ድጋፍ የራሱን ጽህፈት ቤት ባለቤት ለመሆን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ህንፃ ለመግዛትም ጨረታ አውጥቷል።
ፌዴሬሽኑ የህንጻ ግዢውን ለማከናወን ኮሚቴ በማዋቀር እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በምክትል ፕሬዝዳንቱ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም የሚመራው ኮሚቴ ውስጥ ከኮንስትራክሽን እና ከተማ ልማት ሚኒስቴር አንድ መሐንዲስ እንዲሁም ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር አንድ ተወካይ መካተታቸው ታውቋል።
የጨረታ ማስታወቂያው በሪፖርተር እና አዲስ ዘመን ጋዜጦች ላይ የወጣ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ባወጣው መስፈርት መሠረት ከ5 ፎቅ በላይ የሆነ፣ ከ20 በላይ መኪኖችን ማቆም የሚያስችል ስፍራ ያለው እንዲሁም በቦሌ፣ የካ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኝ ህንፃ ባለቤቶች መወዳደር እንደሚችሉ ተገልጿል።
መወዳደር የሚፈልጉ የህንፃ ባለቤቶች የጨረታ ሰነዳቸውን ለቀጣዮቹ 13 ቀናት ማስገባት እንደሚችሉ ሲገለፅ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ላይ ጨረታው የሚከናወን ይሆናል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ስታድየም በሚገኙ ቢሮዎች ሲጠቀም ቆይቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ካዛንችስ አካባቢ ወደሚገኝ ህንፃ ጽህፈት ቤቱን ማዞሩ የሚታወስ ነው።