በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወሳኝ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ሁለተኛው ወራጅ ቡድን የተለየበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎቸ ወላይታ ድቻ ወልዲያን 3-0 በማሸነፍ መቆየቱን ሲያረጋግጥ ኤሌክትሪክ ሲዳማ ቡናን 2-1 ቢያሸንፍም ወልዋሎ እና ድሬዳዋ ሲያደርጉት የነበረው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በመቋረጡ እጣ ፈንታውን ለመወሰን ጨዋታው እስኪያልቅ ይጠብቃል። ድሬዳዋ የተቋረጠው ጨዋታ ነገ ረፋድ ሲቀጥል ካሸነፈ የሚተርፍ ሲሆን ከተሸነፈ እና አቻ ከተለያየ ኤሌክትሪክ የሚተርፍ ይሆናል።
አርባምንጭ ላይ ፋሲል ከተማን የገጠመው አርባምንጭ ከተማ 1-0 ቢያሸንፍም ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ በማሸነፋቸው ምክንያት ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ ተገዷል።
በ2004 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያደገው አርባምንጭ ከተማ እስከ 2007 ድረስ የተረጋጉ የውድድር ዘመናትን ቢያሳልፍም ከዛ ወዲህ ባሉት ጊዜያት በተደጋጋሚ አሰልጣኞትን በመቀያየር እና ወሳኝ ተጫዋቾቹን ማቆየት ባለመቻሉ ላለመውረድ ሲጫወት ቆይቷል። ዘንድሮም በ33 ነጥቦች ከወልዲያ ቀጥሎ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የወረደ ሁለተኛው ቡድን ሆኗል።