ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ሰበታ ላይ ወልዲያን የገጠመው ወላይታ ድቻ 3-0 አሸንፎ ከመውረድ የተረፈበትን ውጤት አስመዝግቧል።

ከሌሎቹ ጨዋታዎች ጋር እኩል ለማስጀመር በኮሚሽነሮች መካከል የስልክ ልውውጥ የተደረገ ሲሆን ከ3 ደቂቃ ቀደም ብሎ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ወላይታ ድቻ የበላይነት የታየበት ነበር። ወልዲያዎች በአንዱዓለም ንጉሴ አማካኝነት በ5ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ሙከራ ሲያደርጉ በ7ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ ለጃኮ ያሳለፈለትን ኳስ ቢያድግልኝ ደርሶ ተደርቦ አቅጣጫውን በመለወጥ ከወልድያ ተከላካይ ጀርባ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው እዮብ አግኝቶ ወደ ግብ አክርሮ ቢመታውም ግብ ጠባቂው አንተነህ ያዳነበት ኳስ በደረቻ በኩል የመጀመርያው ጠንካራ ሙከራ ነበር። በ10ኛው ደቂቃ በድጋሚ ጃኮ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሲያድኑበት በረከት ወልዴ በ15ኛው ደቂቃ በግምት ከ20 ሜትር ላይ አክርሮ የመታው ኳስ ከግቡ አጠገብ የነበረው ቢያድግልኝ ያወጣው ሌላኛው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ድቻዎች ሙከራ ማድረጋቸውን በመቀጠል በ20 እና 27ኛው ደቂቃ የሚጠቀሱ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። በ25ኛው ደቂቃ የወልድያው ግብ ጠባቂ ኳስ ከግብ ክልል ለማራቅ በሚያደርው ጥረት ውስጥ ከጃኮ ጋር በመጋጨቱ ጉዳት አስተናግዶ በምትኩ ደረጀ ዓለሙ ወደ ሜዳ ገብቷል።

በ33ኛው ደቂቃ ኢንተርናሽናል አርቢትር ዳዊት አሳምነው ኳስ በግብ ክልል ውስጥ በቢያድግልኝ ተነክቷል በማለት የሰጡትን አጨቃጫቂ ፍፁም ቅጣት ምት ጃኮ አራፋት ወደግነት ለውጦ ድቻን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላ ወልዲያዎች ክስ አስይዘው በቀጠለው ጨዋታ ወሎዲያዎች ጎል ለማስቆጠር ወደፊት መጓዛቸውን ተከትሎ ድቻዎች የግብ አጋጣሚ ለመፍጠር ክስተት ማግኘት ችሎ ነበር። በተለይ በ40ኛው ደቂቃ እዮብ ዓለማየሁ ግብ ጠባቂውን አሳልፎ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ በግቡ ቀኝ የወጣችበት እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ ከበዛብህ የተሻገረትን ኳስ መሳት በሚከብድ ሁኔታ በግቡ አናት ላይ የሰደዳት ኳስ የሚጠቀሱ ናቸው።
ከዕረፍት መልስ ድቻ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ተጭኖ መጫወት ሲመርጡ ወልዲያዎች መሀል ሜዳ ላይ በቁጥር በመብዛት ኳስ ወደ ግብ ክልላው እንዳይደርስ ሲጥሩ ታይቷል። በ49ኛው ደቂቃ ከመሐል ሜዳው ክፍል ትንሽ አለፍ ብሎ የተገኘውን ቅጣት ምት ውብሸት ዓለማየሁ አክርሮ ወደግብ በመምታት ወደግብነት ለውጦ የድቻ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። በ53ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ኤፍሬም እና አማረን እንዲሁም ግብ ጠባቂውን በማታለል ወደግብ የመታው ኳስ የግብ የቀኝ አግዳሚ ሲመልስበት በ57ኛው ደቂቃ ጃኮ አራፋት የወልዲያ ተጫዋቾች በአግባቡ ያላራቁትን ኳስ ተጠቅሞ ለቡድኑ ሶስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽም ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩት ወልዲያዎች ከዕረፍት መልስ በአንዱዓለም ንጉሴ እንዲሁም በኤደም አማካኝነት ሁለት ጊዜ የጎል ሙከራ ብቻ አድርገዋል። በድቻ በኩል ደግሞ ጃኮን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ዮናታን ከበደ በ87ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው ኳስ የሚጠቀስ ነው።

ጨዋታው በድቻ አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ የጦና ንቦቹ ነጥባቸውን 35 በማድረስ በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ መቆየታቸውን አረጋግጠዋል።