አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከመቐለ ከተማ ጋር ተለያይተዋል

ባደገበት ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ሊጉን 4ኛ በመሆን የጨረሰው መቐለ ከተማ እና ዋና አሰልጣኙ ዮሃንስ ሳህሌ ተለያይተዋል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና ደደቢት አሰልጣኝ ዮሃንስ መቐለን የለቀቁት ውላቸው ሰኔ 30 ከተጠናቀቀ በኃላ ነው፡፡

የአሰልጣኙ ወኪል ድርጅት ኤኤቲ ስፖርትስ ማኔጅመንት የአሰልጣኙን ከመቐለ ከተማ መለያየት ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጧል፡፡ “የአንድ ዓመት ውል ነበረን ከመቐለ ከተማ ጋር፡፡ ይህ ሲጠናቀቅ ከክለቡ ጋር አሰልጣኝ ዮሃንስ ተለያይቷል፡፡ ወደፊት ያለውን ነገር አሁን ላይ መናገር ባይቻልም ከመቐለ ከተማ ጋር ውል በማራዘሚያ ጉዳይ ድርድር አላካሄድንም፡፡” ሲል ኤኤቲ ስፖርትስ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡

በዓመቱ መጀመሪያ መቐለ ከተማን የተረከቡት አሰልጣኝ ዮሃንስ በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እና በፈጣን መልሶ ማጥቃት የሚጫወት ቡድን ገንብተው በፕሪምየር ሊጉ ክለቡ እንዲቆይ አስችለዋል፡፡ ክለቡ ከጅማ አባ ጅፋር (15) በመቀጠል አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ሁለተኛው ቡድን (16) በመሆን ስኬታማ የውድድር ዘመን አሳልፏል፡፡