የመጨረሻው ቀን ትንቅንቅ

(በአብርሀም ገ/ማርያም እና ዮናታን ሙሉጌታ)

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባ ጅፋር የሻምፒዮንነት አክሊሉን ለመድፋት ዛሬ 8፡00 ላይ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን ያደርጋሉ። እኛም በዛሬው ፅሁፋችን በታሪክ እስከመጨረሻው የዘለቁ ፉክክሮች እና የሁለቱ ቡድኖች የውድድር አመት ጉዞ ላይ አተኩረናል።

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አመት ሲነሳ በስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል የተከሰቱ መጥፎ ትዝታዎችን ለማስታወስ መገደዳችን የሚቀር አይሆንም። ነገር ግን አምስት ክለቦችን እስከ መጨረሻዎቹ ጥቂት ሳምንታት ያፎካከረው እና አሸናፊውን ለመለየት እስከ 30ኛው ሳምንት ድረስ እንድንጠብቅ ያደረገን የውድድር አመት መሆኑ አመቱን በክፉ ብቻ እንዳናስታውሰው ያደርገናል። ላለፉት ሰባት የውድድር አመታት መሰል ፉክክሮችን መመልከት አለመቻላችን ደግሞ የዘንድሮው የዋንጫ ፍጥጫ ይበልጥ ትኩረታችንን እንዲስብ የሚያስገድድ ነው። ብርቅ ሆኖ የታየን ይህ ፉክክር ግን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ የመጀመሪያው አይደለም። በርግጥ በአብዛኞቹ አመታት ሻምፒዮኑን ለመገመት የሚያዳግት ፍልሚያ ባንመለከትም ሊጋችን ጨርሶ ፉክክር አልባ ሆኖ የዘለቀም አይደለም። እዚህ ላይ ታሪክ አንገት ለአንገት ተናንቀው አመቱን ስለጨረሱ ቡድኖች ምን እንደሚያሳየን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል።

በ1990 ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ በ8 ክለቦች ሲጀመር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ መድን በእኩል 32 ነጥቦች አጠናቀዋል። ከመድን በ2 ጎል የተሻለ ልዩነት ያስመዘገበው የያኔው መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክም ቻምፒዮን መሆን ችሏል። ከዛ ወዲህ በ1991 እና 1992 እና 1994 ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤሌክትሪክ በ1993 ሳይቸገሩ ዋንጫውን ሲያነሱ በ1995 እና 1996 የሊጉ የልብ ምት ከፍ ያለበት ወቅት ነበር። በ1995 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረገው የመጨረሻው ጨዋታ ለቻምፒዮንነት የ90ኛ ደቂቃ የኤሪክ ሙራንዳ የማሸነፍያ ጎል አስፈልጎት ነበር። በ1996 ደግሞ ልክ እንደዘንድሮው ዋንጫው ሁለት ቦታ ተቀምጦ በተደረጉ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ኒያላን 3-1 አሸንፎ ከኢትዮጵያ ቡና በላይ በማጠናቀቅ ለመጀመርያ ጊዜ የክብሩ ባለቤት ሆኗል። 

ከሁለት ተከታታይ ልብ አንጠልጣይ የመጨረሻ ሳምንት ትዕይንቶች በኋላ ለተከታታይ ዓመታት ሊጉ የአንድ ክለብ የበላይነት ጎልቶ ታይቶበታል። በ1997 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዩ በ18 ነጥቦች ርቆ ቻምፒዮን ሲሆን በ1998 ፈረሰኞቹ ከቡና በ4 ነጥብ ርቀው ደግመውታል። 1999 ላይ በ21ኛው ሳምንት 11 ክለቦች ያቋረጡትን ውድድር ሀዋሳ ከተማ ሲያሸንፍ በ2000፣ 2001 እና 2002 ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀላሉ አሸናፊ ሆኗል። በ2003 የሊጉ ትኩሳት ከዓመታት በኋላ ሲጨምር ሶስት ክለቦች የቻምፒዮንነት ዕድል ይዘው በተደረገው መጨረሻ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና የአሸናፊነት ዘውዱን ደፍቷል። ይህም ከ7 ዓመት በኋላ አሸናፊው በመጨረሻ ቀን የታወቀበት የመጀመርያው ውድድር መሆኑ ነው። ነገር ግን ሊጉ ከ2003 ወዲህ የአጓጊነት መንፈሱን አጥቶ ቆይቷል። በ2004 ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በ2005 ደደቢት፣ ከ2006-2008 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጨረሻው ሳምንት ቀደም ብለው ዋንጫውን ማሸነፋቸውን አረጋግጠዋል።

ከታሪክ ጋር በተያያዘ የሚነሳ ሌላም ግጥምጥሞሽ አለ። ይኽውም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ20 ዓመታት ጉዞ ዘንድሮ ጅማ አባጅፋር ለማሳካት የተቃረበውን ታሪክ እስካሁን አሳክቶ የሚያውቀው አንድ ክለብ ብቻ መሆኑ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ። በ1990 በፕሪምየር ሊጉ ያልተሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በወቅቱ ሁለተኛ የሊግ እርከን በነበረው በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቀዳሚ ሆኖ በማጠናቀቅ ሙገር እና ምድር ባቡርን አስከትሎ ወደ ፕሪምየር ሊግ አደገ። በ10 ክለቦች መካከል በተደረገው ውድድርም በ18 ጨዋታዎች ከተከታዩ ሀዋሳ ከተማ በ8 ነጥቦች ርቆ በ47 ነጥቦች ቻምፒዮን በመሆን ወደ ሊጉ ባደገበት ዓመት ዋንጫ የማንሳት ብቸኛ ታሪክን ፅፏል። ከ19 ዓመታት በኋላ በመጀመርያ የሊግ ተሳትፎው አስደናቂ ጉዞ ያደረገው ጅማ አባ ጅፋርም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ዛሬ አዳማ ከተማን ይገጥማል። ይህን አስደናቂውን ጉዞውን በዋንጫ ካገባደደው ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስን የ1991 ታሪክ የሚደግም ይሆናል።

የዛሬውን የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ስናስብ ሌላው የሚያስገርመን ነገር ቡድኖቹ እዚህ ከመድረሳቸው በፊት ያሳለፉት የውድድር አመት ነው። እንደሁል ጊዜው ለዋንጫው ግምት ተሰጥቶት ወደ ውድድሩ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆነ ከከፍተኛ ሊጉ አድጎ ያልታሰበ አመት ያሳለፈው ጅማ አባ ጅፋር በደረጃ ሰንጠረዡ አናት መገኘት የቻሉት አመሻሹ ላይ ነበር። በውድድሩ መሀል በጣም የተዳከሙባቸው እና የውጤት ማሽቆልቆል ያሳዩባቸው ጊዜያት እንደነበሩም የምናስታውሰው ነው። ምንም እንኳን በቶሎ ሽንፈትን ባያስተናግድም የወትሮው ጥንካሬውን ሳያሳይ ጉራማይሌ ውጤት እያስመዘገበ እስከ 11ኛው ሳምንት የዘለቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሶዶ ላይ በወላይታ ድቻ የአመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ዳግም ወደ ውጤታማነት ለመመለስ ሌሎች አምስት ሳምንታትን ጠብቋል። በነዚህ ጊዜያት ሶስት ግቦችን ብቻ አስቆጥሮ ብዙዎቹን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲያገባድድ በሀዋሳ ከተማ የደረሰበት የ4-1 ሽንፈትም የማይዘነጋ ነበር። ነገር ግን ፈረሰኞቹ መንገዳቸውን በማስተካከል ከዚህ በኃላ 22ኛው ሳምንት ላይ በአርባምንጭ ከተማ 3-0 ከመሸነፋቸው ውጪ 8 ጨዋታዎችን በድል በመደምደም እና በአራቱ ነጥብ በመጋራት ወደላይ ተስፈንጥረዋል። በ28ኛው ሳምንት ወላይታ ድቻን 4-0 ከረቱ በኋላ ደግሞ ሊጉን መምራት ጀምረዋል። 

የጅማ አባ ጅፋር የሊግ ጉዞም ዝቅታዎችን ያስተናገደባቸው ጊዜያት ነበሩ። ከታች ያደገ ክለብ እንደመሆኑ ማንም ከዋንጫ ፉክክሩ ጋር ስሙን ያላነሳው አባ ጅፋር አመቱን በድል ቢጀምርም በመቀጠል የደረሱበት ሶስት ተከታታይ የ1-0 ሽንፈቶች ግን ከጅምሩ ከመውረድ ስጋት ጋር እንዲነሳ አድርጎት ነበር። ነገር ግን በፍጥነት በማገገም በቅዱስ ጊዮርጊስ 10ኛው ሳምንት ላይ እስከተሸነፈበት ሳምንት ድረስ በርካታ ድሎችን በማሳካት ከተከታታይ ሽንፈቶቹ አገግሟል። የመጀመሪያው ዙር እስኪገባደድ ድረስም በተመሳሳይ አኳኋን በመቀጠል በወቅቱ የማይቀመስ ይመስል የነበረው ደደቢትን የአሸናፊነት ጉዞም እስከመግታት መድረስ ችሏል። አባ ጅፋር ሁለተኛውን ዙር ሀዋሳ ላይ በሽንፈት መጀመሩ እንደመጀመሪያው ዙር ወደ ውጤት ማጣት እንዳይወስደው ቢያሰጋም በቀጣይ ሳምንታት ባደረጋቸው ጨዋታዎች ግን ይበልጥ ትኩረትን እየሳበ እና ድሎችን እያስመዘገበ በላይኛው የሰንጠረዡ ፉክክር መርጋት ችሏል። ሆኖም 22ኛው ሳምንት ላይ ሲደርስ ሌላ የውጤት መንሸራተት እንዲገጥመው ግድ ሆነ። በቀጣይ አራት ጨዋታዎች ወይም ከአንድ ወር በላይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ተስኖትም ሰነበተ። ነገር ግን እነዚህ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ እንጂ ሽንፈት የተመዘገባባቸው አልነበሩም።  ወደ አሸናፊነት መመለስ ሲከብዳቸው የማይታዩት አባ ጅፋሮች አሁንም ሶስት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ውጤታቸውን አስተካክለው ሊጉን ለመምራት በቅተዋል። ምንም እንኳን 28ኛው ሳምንት ላይ በተፎካካሪያቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ብዙ ባገባ በሚለው ህግ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ቢገደዱም የሻምፒዮንነት ተስፋቸውን ይዘው ለዛሬው ቀን በቅተዋል።

በዛሬው የውድድር አመቱ የመጨረሻ ቀን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ አዳማ ከተማን ያስተናግዳሉ። አዳማ እና ሀዋሳ የነጥብ ስብስባቸውን ከፍ ከማድረግ ባለፈ የተለየ ግብ የሌላቸው በመሆኑም የአሸናፊነቱ ግምት የተሰጠው ለጊዮርጊስ እና አባ ጅፋር ነው። ነገር ግን አሁን ላይ ከነጥብ ባለፈ በግብ ልዩነትም ጭምር ዕኩል ሆነው ብዙ ባገባ በሚለው ህግ የተለዩት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የመጨረሻ ፈተናዎቻቸውን በድል ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን በርካታ ግቦችንም ማስቆጠር ይጠበቅባቸዋል። ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘ ምንም የቅጣት ዜና የሌለባቸው ክለቦቹ በጉዳት ረገድም ካለፉት ሳምንታት እምብዛም የተለይ ዜና አልተሰማባቸውም። በዚህም መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሰላዲን ሰይድ ፣ አማራ ማሌ እና ሪቻርድ አፒያ እንዲሁም የጅማ አባ ጅፋሮቹ ቢኒያም ሲራጅ እና አሮን አሞሀ በቡድኖቻቸው የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ የማይገኙ ይሆናል። በዳኝነቱ በኩል ደግሞ ኢንተርናሽናል አርቢትር ብሩክ የማነ ብርሀን አዲስ አበባ ላይ ኢንተርናሽናል አርቢትር በላይ ታደሰ ጅማ ላይ በ 08፡00 የጨዋታዎቹን መጀመር እንደሚያበስሩ ይጠበቃል።

በበርካታ አወዛጋቢ ጉዳዮች በታጀበው የውድድር አመት የመጨረሻ ቀን ከ2003ቱ ትዕይንት 7 ዓመታትን ተሻግረን ዘንድሮ ለሌላ የ90 ደቂቃ ትኩሳት ደርሰናል። የዘንድሮውን የሚለየው በነጥብ ብቻ ሳይሆን የግብ ልዩነታቸው ጭምር እኩል ሆነው የተገኙት ክለቦችን እጣ ፈንታ ለመመልከት መዘጋጀታችን ነው። ከ14 ዓመታት በኋላ ሁለት ቦታ ዋንጫ ተቀምጦ የሚደረገው የ30ኛ ሳምንት ማንን የዋንጫ ባለቤት ያደርግ ይሆን? ቅዱስ ጊዮርጊስን ወይስ ጅማ አባ ጅፋርን ?