ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በጎል ልዩነቶች ተበልጦ ቻምፒዮን ሳይሆን ቀርቷል

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአምስተኛ ተከታታይ ጊዜ የሊጉ ቻምፒየን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ፈረሰኞቹ ሀዋሳ ከተማ 2-0 አዲስ አበባ ላይ ቢረቱም በጅማ አባ ጅፋር በግብ ክፍያ ተበልጠው የሊጉን ዋንጫ ክብር ዳግም ሊያገኙ አልቻሉም፡፡

ለወትሮ ጨቅይቶ የነበረው የስታዲየሙ መጫወቻ ሜዳ በዝናብ ምክንያት ውሃ ቋጥሮ ለተጨዋቾች አስቸጋሪ ሁኔታን ልክ ከዚህ ቀደም እንደተደረጉት ጨዋታዎች ፈጥሯል፡፡ በመጀመሪያው 45 ሀዋሳዎች በመከላከል እንዲሁም ጊዮርጊሶች ጫና ፈጥሮ በመጫወት ጥሩ ነበሩ፡፡ ሁሉቱም ክለቦች የጠራ የግብ እድል ለመፍጠር ብዙ ደቂቃ የፈጀባቸው ሲሆን ይበልጥ ወደ መሃል ሜዳ ያደላ እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ተደጋግሞ ይታይ ነው፡፡ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከ18 ሜትር ያገኘውን ክፍተት ተጠቅሞ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ለጥቂት ወጥቶበታል፡፡ ሀዋሳዎች ከዚህ የግብ ሙከራ ውጪ በመጀመሪያው 45 የፈጠሯቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ እንግዶቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በሚደርሱበት ወቅት በውሳኔ ስህተት እድሎቹን ሲያመክኑ ነበር፡፡

ፈረሰኞቹ በፍጥነት ግቦችን ለማስቆጠር ያለመ እንቅስቃሴን በመጀመሪያው አጋማሽ አድርገዋል፡፡ ሆኖም የጠራ የግብ ሙከራ ለማድረግ 27 ደቂቃዎችን መቆየት ግድ ብሏቸዋል፡፡ አብዱልከሪም ኒኪማ ከሳጥኑ ጠርዝ የመታውን ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ከሶስት ደቂቃዎች በኃላ በኃይሉ አሰፋ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ባለሜዳዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ተገቢ ውሳኔ አይደለም በማለት የሀዋሳ ተጨዋቾች የመሃል አርቢትሩ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የፍፁም ቅጣት ምቱ ሳላዲን ባርጌቾ መቶ ግብ ጠባቂው ተክለማሪያም ሻንቆ መልሶበታል፡፡ በ36ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻረገውን ኳስ ሳላዲን ወደ ግብነት ለውጦ ጊዮርጊሶች መምራት ጀምረዋል፡፡ ለእረፍት ከማምራታቸው በፊት ኦስቫልዶ ታቫሬዝ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ፍቅረየሱስ ከመስመር ላይ አውጥቶበታል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታውን መመለስ የሚችሉባቸውን እድሎች ለመፍጠር ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ በ55ኛው ደቂቃ ታቫሬዝ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ሳይደርስባት ሲቀር ከአምስት ደቂቃ በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ብሏል፡፡ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሙሉአለም መስፍን በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ኒኪማ የሞከረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ግብ ጠባቂ ሜንሳ ሶሆሆ ሲያወጣበት በ72ኛው ደቂቃ ታዛሬዝ ያመከነው ያለቀለት እድል የፈረሰኞቹን የግብ መጠን መጨመር የሚችሉ ነበሩ፡፡ ሀዋሳዎች በበኩላቸው በፍሬው ሰለሞን እና ጋብሬኤል አህመድ አማካኝት ያልተሳኩ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

ጨዋታው ወደ መገባደጃው ሲደርስ በተለምዶ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በሚቀመጡበት የግራ ጥላ ፎቅ ክፍል ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ጂራ ላይ ያነጣጠሩ የተቃውሞ እና የስድብ ድምፆች መሰማት ጀምረዋል፡፡ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ደጋፊዎች ወደ አቶ ኢሳይያስ ወንበሮችን እና ቁሶችን ሲወረውሩ የታዩ ሲሆን ፕሬዝደንቱም በፌደራል ፖሊስ ከለላ ጨዋታው ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ስታዲየሙን ለመቀው ለመሄድ ተገደዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በእኩል 55 ነጥብ ሊጉን ቢያገባድም በግብ ክፍያ ተብልጦ በሁለተኛ ደረጃነት ጨርሷል፡፡ ሀዋሳ ከተማ በ36 ነጥብ 9ኛ ደረጃን ይዞ የውድድር ዘመኑን አገባዷል፡፡