በ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ላይ አዳማ ከተማን የገጠመው ጅማ አባ ጅፋር 5-0 በማሸነፍ በመጀመርያ የውድድር ዓመቱ የሊጉ ቻምፒዮን መሆን ችሏል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ለጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች አሚን ነስሩ፣ ተመስገን ገ/ኪዳን እና ኦኪኪ አፎላቢ የሁለት ወር ኮከቦች እና ከፍተኛ ግብ አግቢ ሽልማት ከፋኖ ስፖርት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በጅማ አባጅፋር በኩል ከወላይታ ድቻ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ አሮን አሞሀን በሄኖክ ኢሳይያስ በመቀየር በተለመደው 4-4-2 አሰላለፍ ወደሜዳ ሲገባ በአዳማ ከተማ በኩል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ በቀይ ካርድ ከሜዳ በወጣው ምኞት ደበበ ምትክ ተስፋዬ በቀለን፣ እስማኤል ሰንጋሪን በ በደሳለኝ ደበሽ፣ ቡልቻ ሹራን በሱሌይማን ሰሚድ በመቀየር በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምረዋል።
በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች አባ ጅፋሮች ተጭነው በመጫወት ቶሎ ቶሎ ወደ አዳማ ግብ ክልል በመድረስና ሙከራዎችን በመድረግ የተሻሉ ነበሩ። በ3ኛ ደቂቃ ተመስገን ገ/ኪዳን የአዳማ ግብ ክልል ውስጥ ነፃ ሆኖ ያገኘውን አጋጣሚ ጃኮ ፔንዞ በቀላሉ ሲይዝበት በ5፣ 7 እና 8ኛው ደቂቃዎች ተመስገን፣ ኦኪኪ እና ኄኖክ ኢሳይያስ የአዳማ የግብ ክልል ውስጥ ንፁህ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በ 9ኛው ደቂቃ ኦኪኪ ከመሀል ሜዳ የተሻገረለትን ኳስ በመቆጣጠር ተከላዮችንና ግብ ጠባቂውንም ጭምር በመሸወድ አባጅፋሮችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። በ11ኛው ደቂቃ ተመስገን ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረለትን በግንባሩ ሞክሮ ጃኮ ያዳነበትም የጅማን መሪነት የሚያሰፋ አጋጣሚ ነበር። በአዳማ ከተማ በኩል የተከተሉት በመከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወታቸው ወደፊት ገፍተው እንዳይጫወቱና እድሎችን እብዛም አሰንዳይፈጥሩ አድርጓቸዋል። በ17ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከርቀት የሞከረው ኢላማውን ያልጠበቀ መከራ እና በ20ኛው ደቂቃ ከነዓን ማርክነህ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባሩ የሞከረው በመጀመሪያው አጋማሽ ከፈጠሯቸው እድሎች ተጠቃሽ ናቸው።
ከ20 ኛው ደቂቃ በኃላ አዳማዎች የኳስ ቅብብል ብልጫ ቢወስዱም አባጅፋሮች በረጃጅም ኳሶች የአዳማ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ በመድረስና እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው የሚስቆጩ ነበሩ። በተለይ በ22ኛው ደቂቃ ኄኖክ ኢሳይያስ፣ በ25ኛው ደቂቃ ተመስገን ገ/ኪዳን የሳቷቸው አጋጣሚዎች ይጠቀሳሉ። በ35 ኛው ደቂቃ ዮናስ ገረመው ከግራ መስመር ያሻገረውን ተመስገን ገ/ኪዳን አስቆጥሮ የጅማን መሪነት ወደ 2-0 ከፍ ማድረግ ችሏል። በ45 ደቂቃ የአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዞ በጉዳት በጃፈር ደሊል ተቀይሮ ሲወጣ የመጀመርያው አጋማሽ ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በጅማ 2-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር በእቅስቃሴም በሙከራም ሁለቱም ቡድኖች ተቀዛቅዘው የጀመሩ ሲሆን በ59ኛው ደቂቃ ኦኪኪ የአዳማ ተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም የአባ ጅፋሮችን መሪነት ወደ 3 ከፍ ያደረገች ግብ ሲያስቆጥር በ66ኛው ደቂቃ ኦኪኪ ከዮናስ ገረመው ከግራ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በማስቆጠር አባጅፋርን 4ኛ ግብ በማስቆጠር በግሉ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል። አዳማ ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ወደኋላ ተስበው ለመጫወት የተገደዱ ሲሆን ዳዋ ሆቴሳ ከአዳርጋቸው ያገኘውን ኳስ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ ከወጣችው ሙከራ ውጭ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻለም። በ82ኛው ደቂቃ ተመስገን ገ/ኪዳን ተከላካዮችን አታሎ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የሞከረውን ጃፈር ደሊል ቢመልስበትም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ኦኪኪ ለራሱ 4ኛ ለጅማ 5ግብ በማስቆጠር ጨዋታው በጅማ አባ ጅፋር 5-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ጅማ አባጅፋር ከውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ድሎች አንዱን በማስመዝገብ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በ3 ጎሎች ልዩነት ቻምፒዮን መሆን ሲችል አዳማ ከተማ ከ2005 በወቅቱ ቻምፒዮን ደደቢት 6-1 ከተሸነፈ ወዲህ ከባዱን ሽንፈት አስተናግዷል። ዘንድሮ ወደ ሊጉ ያደገው ጅማ ባደገበት ዓመት ዋንጫ በማንሳት በ1991 ቅዱስ ጊዮርጊስ የሰራውን ታሪክ ሲደግም በ23 ጎሎች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ናይጄርያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ሳሙኤል ሳኑሚ በ2007 በ22 ጎሎች ይዞት የነበረውን በውጪ ዜጋ በአንድ የውድድር ዓመት በርካታ ጎል የማስቆጠር ሪኮርድ ማሻሻል ችሏል።
ጅማ አባጅፋር ቻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ አምበሉ ኤልያስ አታሮ በስፍራው ከተገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም እጅ ዋንጫውን ተቀብሏል። በስታዲየሙ የነበረው ደጋፊ ከመጠን ባለፈ ደስታ ሜዳውን የወረረ ሲሆን በትርምሱ ሁለት ታዳጊዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።