ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በ23 ጎሎች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በበላይነት ማጠናቀቅ ችሏል። ጅማ አባ ጅፋር ከከፍተኛ ሊግ ባደገባት ዓመት ቻምፒዮን ሲሆን የኦኪኪ 23 ግቦች የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል። ቡድኑ በውድድር አመቱ ካስቆጠራቸው ግቦች 59% የሚሆኑት ግቦች የተገኙት ከዚሁ በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ክለቡን ከተቀላቀለው ግዙፉ አጥቂ ነበር። ከትናንቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ኦኪኪ አፎላቢ ከድረገፃችን ጋር የነበረውን አጭር ቆይታ እነሆ።
በኢትዮጵያ ስትጫወት የመጀመሪያህ ነው። ዓመቱን እንዴት አገኘሁ?
ለኔ ጥሩ ነበር። እንዳልከው የመጀመሪያ ነው ኢትዮጽያ ስጫወት። እዚህ በመጫወቴ ደስተኛ ነኝ።
የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በበላይነት ማጠናቀቅ በመቻልህ ምን አይነት ስሜት ፈጠርብህ ?
በጣም ደስተኛ ነኝ። ይህ ስኬት በራስ መተማመኔ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ረድቶኛል። ለዚህ ደግሞ አስተዋፅኦ ያደረጉት የቡድን አጋሮቼን እንዲሁም አሰልጣኜን አመስግናለው።
በኮከብ ግብ አግቢነት ለመጨረስህ ምስጢር የምትለው ነገር ምንድን ነው ?
ምንም ሚስጥር የለውም። ጠንክሬ መስራቴ ብቻ ነው። ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኝ ገብረመድን የሚስጠኝን ምክሮችን እቀበላለው። ብዙ ጊዜ አሰልጣኜ በጨዋታ ላይ እያለው ጠርቶ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ ይነግረኛል። እኔም እሱን እተግብረዋለው። ይህ ነው ሚስጥሩ።
በኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ ለዋንጫ የነበረውን ፉክክርስ እንዴት ተመለከትከው ?
በጣም ከባድ ነበር። ሁላችንም ጠንክረን ከመጫወት ውጪ ምንም አማራጭ የለንም ነበር። እኛ ደግሞ እንደ ቡድን የነበረን እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነበር።
በጅማ አባ ጅፋር ቆይታህ ይቀጥላል ወይስ ቀጣይ ጉዞህ ምን ይሆናል ?
በዚያ ጉዳይ አሁን ላይ ምንም አልልም።
በስተመጨረሻ የምተስተላልፈው መልክት ካለህ?
የቡድን አጋሮቼን ፣ አሰልጣኞቼን እንዲሁም የጅማ ደጋፊ እና ህዝቡን ማመስገን እፈልጋለው። መላው የጅማ ህዝብ ድጋፉ ልዩ ነበር። ከልብ አመሰግናለው።