በሀዋሳ ከተማ ለአራት የውድድር ዘመናት ቆይታ ያደረጉት ያደረገው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከክለቡ ጋር መለያየታቸው እርግጥ ሆኗል።
2007 አጋማሽ ላይ የሱዳኑ አልአህሊ ሸንዲን ለቀው የግማሽ ዓመት ኮንትራት በመፈረም ክለቡን የተቀላቀሉት አሰልጣኝ ውበቱ በቆይታቸው በውጤት ደረጃ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ የሚባል ጊዜን ባያሳልፉም ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያሳይ ቡድን በመስራት እና ለወጣቶች እድል በመስጠት መልካም ስም አትርፈዋል።
በሊጉ በአሁኑ ወቅት ከሚገኙ አሰልጣኞች በአንድ ክለብ ረጅም ጊዜ በመቆየት ቀዳሚ የነበሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዛሬ ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ቡና ጋር በኢትዮጵያ ዋንጫ ተጫውቶ ሽንፈትን ካስተናገደ በኃላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከክለቡ ጋር በይፋ መለያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ከክለቡ ጋር ጥሩ ጊዜን አሳልፌያለሁ። በጋራ በርካታ ነገሮችን መስራት ችለናል። አሁን ላይ ከሀዋሳ ጋር ተለያይቼ አዲስ ፈተና መቀበል አለብኝ። በሀዋሳ በርካታ ስራዎችን ሰርተናል። ለምሳሌ ክለቡ ከሌላ ቦታ የሚያመጣቸውን ተጫዋቾች ከፊርማ ጋር በተያያዘ ቅድመ ክፍያን ስለሚፈልጉ የመጨረሻ የሚባሉ ተጨዋቾችን ለማምጣት እንገደድ ነበር። ለዚህም ምክንያቱ ከቅድመ ክፍያ ጋር በተያያዘ በዛ ደረጃ ተጫዋች አምጥተህ ከታች ልጅ አሳድገህ ቡድን መገንባት ከባድ ነው። እኛ ደግሞ በየአመቱ እያፈረስን እየገነባን፣ ተጫዋቾችንም ማቆየት አልቻልንም። ዘንድሮ ግን ጥሩ ነገር ሰርተናል። ወጣቶቹ ማደጋቸው ትልቅ ነገር ነው። ማሳደግ ብቻ ሳይሆን እኚህ ተጫዋቾች ተጨማሪ ኮንትራት እንዲፈርሙ አድርገናል። እኔ ከሰራሁት መሀል ይህ ጥሩ ስራ ብዬ የምወስደው ነው። በዚህ በጣም እኮራለሁ። ሀዋሳ የሊጉን ዋንጫ ያነሳ ትልቅ ክለብ ነው። በዚህ ክለብ መስራቴን ሳስበው ያስደስተኛል። ” ብለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አክለውም ” በተለያዩ ጊዜያት ከጎኔ ለነበሩት ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት፣ የክለቡ አመራሮች፣ ደጋፊዎች እና ላልተለዩኝ በሙሉ ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ። ” ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ታጭተው የነበሩት አሰልጣኙ ቀጣይ ማረፊያቸው በቅርቡ ይታወቃል ተብሎ ሲጠበቅ ፋሲል ከተማ ማረፊያቸው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ሀዋሳ ከተማ በአንፃሩ ምክትል አሰልጣኙ ሙሉጌታ ምህረትን ለመቀጠር መቃረቡም ተሰምቷል፡፡