የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዚህ ሳምንት በርካታ ጨዋታዎች ተከናውነዋል። ከጨዋታዎቹ ጋር አያይዘን አዳዲስ መረጃዎችን እንዲህ አጠናቅረናል።
የምድብ ሀ ጨዋታዎች
በምድብ ሀ 25ኛ ሳምንት ባህርዳር እና ሽረ ድል አስመዝግበዋል። የምድብ ሀ አናት ላይ የተቀመጠው ባህር ዳር ከተማ በባህርዳር ደርቢ አውስኮድን ገጥሞ ከመመራት በመነሳት 3-1 አሸንፏል። ሙሉቀን ታሪኩ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር በሁለተኛው ዙር የተነቃቃው ፍቃዱ ወርቁ ቀሪውን ጎል አስቆጥሯል። ምድቡን ባህርዳር በ57 ነጥብ ከተከታዩ ሽረ በ10 ነጥቦች ርቆ ምድቡን እየመራ ይገኛል።
ከነቀምት ጋር ጨዋታውን በአዲስ አበባ ያደረገው ሽረ እንዳሥላሴ ልደቱ ለማ በ18ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ጎል 1-0 በማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃውን አጠናክሯል። አዲስ አበባን ከወሎ ኮምበልቻ ያገናኘው ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅ በተመሳሳይ ሰበታ ከ ለገጣፎ እና ኢኮስኮ ከ ቡራዩ ያለምንም ጎል የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው። ኢትዮጽያ መድን በጌትነት ተስፋዬ ሁለት ግቦች እንዲሁም በሀብታሙ መንገሻ ግቦች ታግዞ ደሴ ከተማን 3-2 ሲያሸንፍ የካ ክፍለከተማ ሱልልታ ከተማን 1-0 በማሸነፍ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል።
አአ ከተማ ፎርፌ ተወስኖበታል
አዲስ አበባ ከ ፌደራል ፖሊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ የተጫዋች ተገቢነት ክስ አስመዝግቦ የነበረው ፌዴራል ፖሊስ የፎርፌ ውሳኔ እንዳገኙ ታውቋል። የክለቡ የቡድን መሪ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ክሱ ውሳኔ ያገኘ መሆኑን ገልፀው 3 ነጥብ እና 3 ንፁህ ጎል ለፌደራል ፖሊስ ተወስኗል። ይህን ጨዋታ አአ ከተማ 5-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ከውሳኔው በኋላ ሰንጠረዡ ይህን ይመስላል:-
የምድብ ለ ጨዋታዎች
በ23ኛ ሳምንት የምድብ ለ ተስተካካይ ጨዋታ ሀምበሪቾን የገጠመው ሀላባ ከተማ 3-0 አሸንፏል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች በሀላባ ስታድየም ዙርያ የችግኝ ተከላ ሲያከናውኑ በሜዳ ላይም ጨዋታው ከመጀመሩ ቀደም ብሉ የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች አንድ ላይ በመሆን ለደጋፊዎች ሰላምታን ሰጥተዋል።
ብዙም ሳቢ ባልነበረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሀላባ ከተማዎች ኳስ ይዞ ተጭኖ በመጫወቱ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በ3ኛው ደቂቃ ስንታየሁ መንግስቱ ከፉአድ አቢኖ መሀል ለመሀል የተሻገረለትን ኳስ ሳይጠቀምበት የቀረበት እንዲሁም በተመሳሳይ በ5ኛው እና በ11ኛ ደቂቃ ላይ ተመሳሳይ ለግብ የቀረቡ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ናቸው። ፍጹም ደስ ይበለው ከሰዒድ ግርማ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ የመታትና በሀላባው ግብ ጠባቂ ሶፍያን ኑረዲን የመከነችው ኳስ በሀምበርቾዎች በኩል ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። በ13ኛው ደቂቃ ከግቡ በግምት ከ25 ሜትር አካባቢ የተሰጠውን ቅጣት ምት አብነት ወደግብነት ቀይሮ ሀላባን መሪ ሲያደርግ በ19ኛው ደቂቃ ስንታየው መንግስቱ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ወደግብነት በመቀየር የሀላባን መሪነት ወደ 2 ከፍ ማድረግ ችሏል። ከግቦቹ መቆጠር በኋላ የመጀመርያው አጋማሽ እስኪጠናቀቅ ለተመልካች አሰልቺ የሆነ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ሀምበርቾዎች ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ የተሻሉ ቢሆኑም ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሽኩቻ እና ኃይል በተቀላቀለበት አጨዋወት የታጀበው የሁለተኛው አጋማሽ ሀምበርቾዎች ሰኢድ ግርማን በመቀየር የአጥቂ ቁጥራቸውን ጨምረው ቢጫወቱም 75 ደቂቃዎች እስኪቆጠሩ ድረስ እምብዛም የግብ ሙከራ አልታየም። በሀላባዎች በኩል በ75ኛው ደቂቃ ስንታየውን ቀይሮ የገባው ሆጴ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ዳግም የመለሰ ሆኖ በተደጋጋሚ ጫና ፈጥሮ መጫወት ችለው መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪው ደቂቃ ላይ አቦነህ ገነቱ ከፉአድ አቢኖ የተሻገረለትን ኳስ በአግባቡ ወደ ግብነት በመቀየር ጨዋታው በሀላባ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሀላባዎች በቀጣይ የ24ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸውን ከመቂ ከተማ ጋር ሐምሌ 17 ላይ ያደርጋሉ።
የምድቡ 25ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀመር ናሽናል ሴሜንት በፋሚ እስክንድር ጎል መቂ ከተማን 1-0 አሸንፏል። ነገ ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ቤንች ማጂ ከ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ ከ ቡታጅራ ከተማ፣ ስልጤ ወራቤ ከ ከተማ በተመሳመይ 04:00 የሚጫወቱ ይሆናል።
የዲላ ከተማ ተጫዋቾች ቅሬታቸውን አሳምተዋል
(በቴዎድሮስ ታከለ)
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደረግ እየተፎካከረ የሚገኘው ዲላ ከተማ ያለፉትን ሶስት ወራት ለተጫዋቾቹ የደመወዝ ክፍያ እና ጥቅማጥቅም እንዳላገኙ የቡድኑ ተጫዋቾች ለሶከር ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የዲላ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ብለዋል፡፡ ” የተባለው እና ተጨዋቾቹ ያነሱት ቅሬታ ተገቢ ነው። የቡድኑ የፋይናንስ ችግር በአካባቢው በተፈጠረው ያለመረጋገት የተፈጠረ ችግር ነው። የፋይናንስ ችግሩን በሂደት ለመፍታት የሚቻለንን ጥረት እያደረግን ነው። ከመንግሥት ድጎማ የሚገኝ በመሆኑ በትዕግስት መጠበቁ ግድ ይላል።” ሲሉ ገልፀዋል። በዚህ ረገድ የክለቡ ውጤታማነት ላይ ተፅኖ አያመጣም ብለን ላነሳነው ጥያቄ ስራ አስኪያጁ ሲመልሱ “ምንም አይነት ተፅዕኖ ያመጣል ብለን አናስብም። አስቀድመን ለአሰልጣኙ ጉዳዩን ገልፀን ተጫዋቾቹ ክለቡን እያገለገሉ ክፍያውን እንፈፅማለን ተባብለናል። ይህን የደመወዝም ሆነ የኢንሴንቭ ችግራችንን ፈትተን በዚህ ወር በሙሉ ክፍያቸውን ለማጠናቀቅ ከሚመለከተው ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው። በሂደትም ይህ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ጥንቃቄ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን።” ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡