ፋሲል ከተማ የአዲሱ አሰልጣኙን ቅጥር እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ዛሬ ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል።
ከተጠራበት ሰዓት ዘግየት ብሎ በጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የክለቡ ሶስት የቦርድ አባላት እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በአንድነት በመሆን ለአንድ ሰዐት ያህል በስፍራው ከተገኙ ጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል። በመርሀ ግብሩ መጀመሪያ ስለክለቡ ወቅታዊ ሁኔታ ገለፃ ያደረጉት የክለቡ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስቻለው ወርቁ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በገለፃቸውም የክለቡን ደረጃ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስረድተው ከስያሜው በመጀመርም የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ በሚል መጠሪያ እንዲጠቀም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በተወሰደ ተሞክሮ የክለቡን መዋቅራዊ አደረጃጀት በመቀየር ለስራ አኪያጅ እንዲሁም ለቴክኒክ እና አስተዳደር ክፍሎች የሚሆኑ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች በቅጥር የሚገቡበት መስፈርት እንደተዘጋጀ አስረድተዋል።
በቀጠል አቶ አስቻለው የዚሁ ለውጥ የመጀመሪያ እርምጃ ለሆነው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቅጥር ምክንያት የሆኑ ነገሮችን አስረድተዋል። እንደሳቸው አገላለፅ አሰልጣኙ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ ካሉ ስመጥር እና ብቃት ያላቸው አሰልጣኞች አንዱ በመሆናቸው ክለቡን ካለበት ደረጃ ከፍ ያደርጋሉ ብለው እንዳመኑ እና በጎንደር እና በአካባቢው ያሉ ወጣቶችን በማብቃት ወደ ትልቅ ተጨዋችነት ማሳደግ ላይም የራሳቸው አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ በማሰብ እንዲሁም የደጋፊውን ጥሩ እግር ኳስ የሚጫወት ውጤታማ ቡድን የማየት ህልም እንደሚያሳኩ በማመን ቅጥሩን መፈፀማቸውን አስረድተዋል። ” ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በሰበሰብነው መረጃ አሰልጣኝ ውበቱ በደጋፊዎቻችን ተቀባይነት አላቸው። እንደ ዕድል ሆኖ የቀደሙት አሰልጣኛችን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም በሙያው ስነምግባር የታነፁ እና ተግባብተው መስራት የሚችሉ ነበሩ። አሁን ደግሞ ቡድኑ ከሚፈልገው ውጤት አንፃር አቶ ውበቱን ለአሰልጣኝነት መርጠናል።” ያሉት ምክትል ሰብሳቢው ስለቀጣይ ዕቅዶች ሲናገሩም ” በቀጣይነት አሰልጣኝ ውበቱ ስራቸውን ከጀመሩ በኋላ ክለቡን ማጠናከር ቀዳሚ ስራችን ይሆናል። የፋይናንስ አቅማችንን ለማጎልበት የገቢ ማሰባሰቢያ እና ሌሎች አማራጮችንም እንተገብራለን። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ያለንበትን ክፍተቶች ባማከለ ሁኔታም ተጨዋቾችን እናስፈርማለን። በቀጣይም እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ወደ ኤርትራ ተጉዘን ለምናደርገው የወዳጅነት ጨዋታም እንዘጋጃለን።” ብለዋል።
ቀጥሎ ንግግር የማድረግ ዕድል ያገኘው ዋንጫ የማንሳት እና መገለጫ ያለው አጨዋወትን የሚከተል ቡድን የመገንባት ሀላፊነት የተጣለበት አሰልጣኝ ውበቱም ” ከሐምሌ 1 ጀምሮ ወደ ፋሲል ለመምጣት ተስማምቻለው። የተለያዩ ጥያቄዎች ቢደርሱኝም ቀጣይ ማረፊያዬን ረጋ ብዬ በማሰብ ጠንካራ ደጋፊ ያለው እና እኔ ለምመርጠው አጨዋወት የሚመቹ ነገሮችን ያሟላ ክለብ መሆኑን ተገንዝቤ ቀጣዮቹን ሁለት አመታት አብሪያቸው ለመቆየት ወስኛለው። በዚህም ደስታ ይሰማኛል። በቆይታዬም ከአመራሩ ጋር በመተባበር የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ጥረት አደርጋለው። ለኔም ለክለቡም መልካም የስራ ጊዜን እመኛለሁ። ” በማለት በወር የተጣራ ስልሳ ሽህ ብር እና በድርድር ላይ ያሉ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ስለሚያስገኝለት አዲሱ ስራው ተናግሯል።
ከዚህ በኋላ ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን የቦርድ አመራሮቹ ምላሾችን ሰጥተዋል። ወጣቶችን የማሳደግ ስራ ከአሰልጣኙ የስራ ጊዜ ማጠር ጋር ሊተገበር የሚችልበት መንገድ ላይ ለተነሳው ጥያቄ በስፍራው ካሉ ፕሮጀግቶች ጋር ቀርቦ የሚሰራ እና ለታዳጊዎች የእድገት መንገዱን የሚያመቻች የቴክኒክ ዳይሪክተር ቅጥር እንደሚፈፀም የተነገረ ሲሆን ሌላኛው የቦርድ አባል አቶ እሸቱ ያድጎ ባነሱት ሀሳብም ” ከአሰልጣኙ ጋር የሚኖረን ቆይታ በሁለት አመት የሚቋጭ አይሆንም። በቀጣይ ጊዜያትም ውል የማራዘም አማራጭ አለን። አሁን ባለው ሁኔታ ከታች በሚመጡ ተጨዋቾች ብቻ ውጤት ማምጣት ከባድ ነው። ስለዚህም ባሉን ተጨዋቾች በይሸፈኑ ቦታዎች ላይ ግዢዎችን እንፈፅማለን። በሂደት ግን ወጣቶችን በማሳደጉ ላይ እናተኩራለን። ምንም አይነት አማራጭ ካላገኘን በቀር ግን ተጨዋቾችን ከውጪ የማምጣት ሀሳብ የለንም። ይሉትም ከጥቂቶቹ በቀር ከክለቡ ጋር አይቀጥሉም። ” ሲሉ ተደምጠዋል።
ለተጨዋቾች በሚያወጡት የተጋነነ ክፍያ ምክንያት ክለቦች ላይ እየተፈጠረ ካለው ጫና አንፃር የፋሲልን ዝግጅት ምን እንደሚመስል ተጠይቀው የመለሱት አቶ አስቻለው ደግሞ ” የክለባችን የፋይናንስ ምንጮች ከተማ አስተዳደሩ እና ወረዳዎች ፣ ስፖንሰሮቻችን እንዲሁም የደጋፊ ማህበሩ መዋጮ ናቸው። ከነዚህ ውጪም በሌሎች ገቢ የማሰባሰቢያ ሂደቶች ራሳችንን እናጠናክራለን። አሁንም ባለን አቅም ልክ ነው ውሎችን የምንፈፅመው በመሆኑም ጫና አይኖረውም። በተጨዋቾች ዝውውር ጉዳይ ላይ ለመወሰን ደግሞ የክለቦችን እና የገበያውን አካሄድ በማየት ላይ እንገኛለን። ” ብለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱም ለሱ በተነሱት ጥያቄዎች ዙሪያ እንዲህ ሲል ጠቅለል ባለ መልኩ ምላሽ ሰጥቷል። ” ለአራት አመት ኮንትራት ነበር ያናገሩኝ። ሆኖም እኔ አልተቀበልኩትም። በርግጥ አንድ ቦታ ላይ መቆየት የተሻለ ስራ ለመስራት ይረዳል። ነገር ግን የፌዴሬሽኑ የአሰልጣኞች ውል ብዙ ነፃነት አይሰጥም። የስራ ዋስትናንም የሚፈታተን ስለሆነ በረጅም ጊዜ ውል መታሰርን ከባድ ያደርገዋል። ሆኖም በየትኛውም ጊዜ ለማራዘም ውሉ የሚሰጠን ክፍተት አለ። ታዳጊዎችን በተመለከተ እኔ መሰረቱን የመጣል ድርሻ ነው ያለኝ ከዛ ግን እኔ ብቆይም ባልቆይም ክለቡ ሊያስቀጥለው ይችላል። በተረፈ ምክትል አሰልጣኞቼን በራሴ የመምረጥ ነፃነት ተሰጥቶኛል። በሀገራችን ባለው ሁኔታ ምክትል አሰልጣኞች ለዋና አሰልጣኞች አለመረጋጋት ምክንያቶች ናቸው። እንደሌላው አለም አሰልጣኝ ሲወጣ አብረው ስለማይወጡ ለነሱ የስራ ዕድል እንደመክፈት የሚታይ ነው። ስለዚህ ይህ ነፃነት ሲሰጠኝ አብረውኝ በሙሉ ሀላፊነት ከሚሰሩ ችግር ሲኖር ደግሞ አብረውኝ ከሚሰናበቱ ሰዎች ጋር ነው የምሰራው። በስራ ህይወቴ በርካታ ደጋፊዎች ካላቸው ክለቦች ጋር ስለሰራው ጫና ውስጥ አልገባም። ”
የዕለቱ መርሀ ግብር ከመጠናቀቁ በፊትም ሁለቱ አካሎች ውሉን የተፈራረሙ ሲሆን አሰልጣኙም የክለቡን አርማ ይዘው ፎቶ ተነስተዋል።