የሲሸልሱ ጨዋታና የአጥቂዎቻችን ነገር


አስተያየት በ ዮናታን ሙሉጌታ


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2017 አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ሁለተኛ ጨዋታ ከሲሸልስ አቻው ጋር አድርጎ ነጥብ ተጋርቶ መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡ ውጤቱንም ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ ከሁሉም የሚልቀው ግን አጥቂዎቻችን የባከኑት የግብ እድሎች ብዙ መነጋገርያ ፈጥሯል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስን ጨምሮ ሚድያዎች እና ተመልካቾች ለአቻ ውጤቱ የአጥቂዎችን ግብ ማምከን እንደምክንያት ጠቅሰዋል፡፡

ጌታነህ እና ሳላዲን የሚጠበቅባቸውን ባለመፈፀማቸው ቡድኑ አቻ እንዲወጣ እንደ አንድ ምክንያት እንጂ እንደ ብቸኛ ምክንያ አድርጎ አጥቂዎቹን መውቀስ አያስፈልግም፡፡ ቡድኑ የአጨዋወት ባህርዩ ፣ የተጋጣሚው ያልተገመተ አቋም እና ከሜዳ ውጪ መጫወቱ ነጥብ እንዲጥል ከአጥቂዎቹ ግብ ማምከን ጋር ተደማምሮ ሊቀርብ ይገባዋል፡፡ አጥቂዎቻችን ላይ ጣታችንን ከመቀሰር ባለፈ ግብ ለማስቆጠር ያልቻሉበትን ምከንያት እና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሄ ሀሳቦችን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

 

የመሰለፍ እድል እና ስነ – ልቡና

የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያ አጥቂ የሆነው ጌታነህ ከበደ ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ካደረጋቸው ሶስት ጨዋታዎች መካከል በጎልደን አሮውስ 1 ለ 0 ሲሸነፉ ያልተሰለፈ ሲሆን ከዛ በኋላ በተደረጉት ጨዋታዎች ማለትም ፖልክዋኔ ሲቲን 3ለ0 ሲያሸንፉ እንዲሁም በቺፓ ዩናይትድ 4ለ0 ሲሸነፋ ለ84ና 58 ደቂቃ በቅደም ተከተል ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

የብሔራዊ ቡድናችን አምበል ሳልሀዲን ሰይድም በተመሳሳይ ቡድኑ ኤምሲ አልጀርስ ከፓያ ሶውራ ጋር 0ለ0 ሲለያይ ሙሉ ለሙሉ ያልተሰለፈ ሲሆን ሬሊዝን 2-1 ሲያሸንፉ በሁለተኛው አጋማሽ እንዲሁም ኤምሲ ሶውራን ገጥመው 0ለ0 በጨረሱበት ጨዋታም ከ65ኛው ደቂቃ ጀምሮ ተጯውቷል፡፡ በዚህ መሰረት ሁለቱ አጥቂዎቻችን በየክለባቸው ከመጨረሻዎቹ 270 ደቂቃዎች ሳላዲን 70 ደቂቃዎች እንዲሁም ጌታነህ 140 ደቂቃዎች ተሰልፈው ተጫውተው ጎል አላስቆጠሩም፡፡

ጌታነህ በቀድሞ ክለቡ ቢድቬትስ ዊትስ እምብዛም የመሰለፍ እድል አልተሰጠውም ነበር፡፡ በ2014/15 የውድድር ዘመን ከ12 ጨዋታ በላይ የመጫወት እድል ያልተሰጠው ሲሆን አብዛኛውን ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ አድርጎ ያስቆጠረው ግብ 2 ብቻ ነው፡፡ ሳላዲን ሰኢድም በአል አህሊ በውድድር ዘመኑ 17 ጨዋታዎች ላይ ብቻ የተሰለፈ ሲሆን ያስቆጠረውም 4 ግብ ብቻ ነው፡፡ ሳላ በጉዳት በርካታ ጊዜ ከጨዋታ ውጪ ሆኖ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን አጥቂዎቻችን በቂ የመሰለፍ እድል ካለማግኘታቸው ጋር የተያያዘ የስነ-ልቡና ፣ የአእምሮ ዝግጁነት እና አካል ብቃት ችግር ሰለባዎች መሆናቸውን ነው፡፡

አጥቂዎች ግብ የማስቆጠር ብቃታቸው ከስነ-ልቡና እና በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ከማስቆጠር ጋር ይያያዛል፡፡ በጥሩ ግብ የማስቆጠር አቋም (form) ላይ ያለ አጥቂ በቀጣዩ ጨዋታ ግብ የማስቆጠር ስነ-ልቡናዊ አቅሙ ይጨምራል፡፡ በተከታታይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለ አጥቂ ደግሞ በተቃራኒው በቀጣዩ ጨዋታ ግብ ለማስቆጠር ይቸገራል፡፡

ጌታነህ ከበደ በስነ-ልቡናው እና በአካል ብቃቱ ረገድ ዝግጁ አለመሆኑን በሌሶቶው ጨዋታ በሚገባ ተመልክተናል፡፡ ተጫዋቹ ወደ ቀድሞው አስፈሪ አቋሙ እንዲመለስ በቋሚነት መሰለፍ እና ግቦች ማስቆጠር ይጠበቅበታል፡፡ ጥሩ አቋም ላይ በማይገኝባቸው ወቅቶች ከምርጫ በመዝል ተጫዋቹ በድጋሚ ለብሄራዊ ቡድን ለመመረጥ ጠንክሮ እንዲሰራ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

እንደጌታነህ ባይሆንም ሳላዲን ሰኢድ አካል ብቃቱ እና የጨዋታ ዝግጁነት ደረጃው እንደቀድሞው አይደለም፡፡ የሳላ የተለየ የሚያደርገው ጥሩ ባልሆነባቸው ጨዋታዎችም ቡድኑን ሲታደግ መስተዋሉ ነው፡፡ ለአብነትም የሌሶቶው ጨዋታ እንደ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡

248862hp2

ከውጭ የሚመጡት ተጫዋቾች በወዳጅነት ጨዋታዎች ሊካተቱ ይገባል

በቅርብ አመታት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ሲያደርግ ከውጭ የሚመጡት ተጫዋቾች ተሳታፊ አይደሉም፡፡ በኛ ሃገር የተለመደው የሃገር ውስጥ ተጫዋቾችን ሰብስቦ ለረጅም ጊዜ በማዘጋጀትና የሚገኘውን ጥቂት የአቋም መለኪያ ጨዋታ በማጫወት የነጥብ ጨዋታ ሲቃረብ የውጭ ተጫዋቾችን መቀላቀል ነው፡፡

ከውጭ የሚመጡት ተጫዋቾች ካለ በቂ ውህደት በነጥብ ጨዋታዎች ላይ በቀጥታ የሚሰለፉ በመሆናቸው የአጥቂዎቻችን ችግርም ከዚህ ሊለይ አይችልም፡፡ ፌዴሬሽኑ ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታ ካሌንደሮችን ተጠቅሞ የወዳጅነት ጨዋታ በማድረግ ተጫዋቾቻን የበለጠ እንዲዋሃዱ ማድረግ የተሸለ ነው፡፡ እነ ሳላዲንም በተደጋጋሚ የወዳጅነት ጨዋታዎች እድል ሲያገኙ ግብ ወደማስቆጠር ብቃታቸው ሊመለሱ ይችላል፡፡

 

አጨዋወት

የብሔራዊ ብድኑ በሌሶቶው አሁን ደግሞ በሲሸልሱ ግጥሚያ የመረጠው የጨዋታ አቀራረብና የተጫዋቾች አመራረጥ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄን አስከትሎ አልፏል፡፡ በተለይም ከጨዋታው በፊት ቡድኑ ይዞት ይገባል የተባለው የ4-4-2 ቤተሰብ (variant) የሆነው 4-3-1-2 / 4-1-3-2 ፎርሜሽንን ተጫዋቾች ለመተግበር ተቸግረው ታይተዋል፡፡ የመሀል ክፍሉን ከጋቶች ፓኖም ግራና ቀኝ ይዘው የተሰለፋት ዑመድ ኡኩሪ እና ኤፍሬም አሻሞ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ከመሆናቸው አኳያ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል እንዲሁም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያረገው ሽግግር ወቅት ግርታ ተስተውሎበታል፡፡ ይህም በተደራጀ ሁኔታ ለአጥቂዎች የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ እንዳይፈጥር አድርጎታል፡፡

ቡድኑ በተጠና ሁኔታ ወደ ግብ ከመድረስ ይልቅ በዘፈቀደ በሚላኩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሲጥር ታይቷል፡፡ ቡድናችን ወጥ የሆነ የጨዋታ አቀራረብ ያልነበረው በመሆኑ ለአጥቂዎቻችን ትክክለኛ ኳሶች ሲደርሷቸው አልተመለከትንም፡፡ ቢደርሳቸው እንኳን በዘፈቀደ በሚላኩ ኳሶች በመሆናቸው አጥቂዎች በጥሩ አቋቋም ላይ ሆነው ወደ ግብ ሊሞክሩ አልቻሉም፡፡

 

ለሌሎች አጥቂዎች እድል መስጠት

በእርግጥ በብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ሃገር በቀል አጥቂዎች የነጌታነህን ያህል ልምድ እና የጥራት ደረጃ ባይኖራቸውም በጥሩ አቋም ላይ ያሉ አጥቂዎችን በመጫወት እድል መስጠት ይገባናል፡፡

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በተደጋጋሚ እንደሚናገሩት ከውጭ የሚመጡ ተጫዋቾች አቋማቸው ምንም ይሁን ምን ከማሰለፍ ውጪ አማራጭ የላቸውም፡፡ አሰልጣኙ ይህን ቢሉም የመጫወት ዝግጁነት የሌላቸውን አጥቂዎች ከማሰለፍ ሌሎች አማራጮችን መመልከት የተሻለ ይሆናል፡፡ ሃገር ውስጥ ያሉት አጥቂዎች አብረው የቆዩ በመሆናቸው የተሻለ ሊዋሃዱም ይችላሉ፡፡

ያጋሩ