ሀዋሳ ከተማ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቻምፒዮን ሆኗል

በባቱ ከተማ ያለፉትን 10 ቀናት ሲከናወን የቆየው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በዛሬው እለት ሲጠናቀቅ ሀዋሳ ከተማ ለ3ኛ ተከታታይ የውድድር ዓመት ቻምፒዮን የሆነበትን ድል አስመዝግቧል።

03:00 ላይ ከፍፃሜው ጨዋታ በፊት ለደረጃ የተጫወቱት አፍሮ ፅዮን እና ወላይታ ድቻ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1-1 በሆነ ውጤት በማጠናቀቃቸው በቀጥታ ወደ መለያ ምት አምርተው ወላይታ ድቻ 5-3 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

05:20 ላይ የተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን 3-2 ማሸነፍ ችሏል። በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች የእንቅስቃሴ ብልጫ የወሰዱት ሀዋሳ ከተማዎች ብልጫቸውን በጎል ለማጀብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ14ኛው ደቂቃ አጥቂው መስፍን ታፈሰ በቀኝ መስመር ገፍቶ በመግባት ያሻማውን ኳስ ምንተስኖት እንድሪያስ ወደግብነት ለውጦ ሀዋሳን መሪ መሆን ችሏል። ከጎሉ በኋላ አዳማ ከተማዎች የግብ ልዩነቱን ለማጥበብ አጥቅተው የተጫወቱ ሲሆን ኳስ በማራኪ ፍሰት ወደ ተጋጣሚያቸው ሳጥን በተደጋጋሚ ማድረስ ችለው ነበር። በተለይ በ24ኛው ደቂቃ ፍሬ ለማፍራት ከጫፍ ደርሰው አቤል ደንቡ ያባከነው የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነው። አዳማዎች የግብ ክልላቸውን ለቀው በሚወጡበት ወቅት የሚፈጠረውን ክፈተት ለመጠቀም ሲጥሩ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በረጅም ኳሶች ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በ34ኛው ደቂቃም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ምንተስኖት እንድሪያስ በአግባቡ ተቆጣጠሮ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ወደግብነት ተለውጦ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል።

አዳማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ባደረጉት ጥረት በ39ኛው ደቂቃ ደግሞ ከቀኝ መስመር ፍቅር ደመላሽ ያሻገረውን ኳስ አቤል ደንቡ አስቆጥሮ ልዩነቱን ቢያጠብም የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቂቂያ ላይ በረከት ካሌብ ከአቤኔዘር መላኩ የተሻገረለትን ኳስ ብቻውን ወደፊት በመግፋት ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን በድጋሚ በማስፋት በሀዋሳ 3-1 በሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ሙሉ በሙሉ አዳማ ከተማ ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን በአንፃሩ ሀዋሳዎች በመከላከል እና የጨዋታውን እንቅስቃሴ በማዘግየት ላይ ተጠምደው ተስተውሏል። በአዳማ ከተማ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቢንያም በ79ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ አንድ ቢያጠብም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት በሀዋሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሀዋሳ ከተማም ለሶስተኛ ተከታታይ ዓመት ቻምፒዮን መሆን ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሆኑት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እና አቶ ሰውነት ቢሻው አማካኝነት የሜዳልያ እና የዋንጫ ስነስርዓት ተከናውኗል።