የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በባቱ ከተማ መካሄዱን ቀጥሎ ዛሬ በተካሄዱ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ፍፃሜ ተሸጋግረዋል።
8:00 ላይ በባቱ ስታድየም የተካሄደው የደደቢት እና የወላይታ ድቻ ጨዋታ በድቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ በግብ ሙከራ ተሽለው የታዩት ወላይታ ድቻዎች ነበሩ። በደደቢት በኩል በ7ኛው ደቂቃ ምስጋናው መኮንን ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡሽ አበራ ያዳነበት የጨዋታው የመጀመርያ መከራ ነበር። በድቻ በኩል ደግሞ በ13ኛው ደቂቃ በረከት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ስንታየው ያዳነበት እንዲሁም ታምራት ለገሰ እና ምስክር መለስ ያደረጉት ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። ከዕረፍት መልስ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ወላይታ ድቻዎች በ52ኛው ደቂቃ ሳምሶም ደጀኔ እና በ72ኛው ደቂቃ ታምራት ለገሰ ባስቆጠሯቸው ጎሎች 2-0 ሲመሩ ደደቢት ከመሸነፍ ያልዳነበት ብቸኛውን ግብ በ83ኛው ደቂቃ ምስጋናው መኮንን አስቆጥሮ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአምናው ቻምፒዮን ሀዋሳ ከተማን የገጠመው ኢትዮጽያ ቡና በመለያ ምቶች አሸናፊ በመሆን ለፍፃሜው አልፏል። ብዙም ማራኪ ባልነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጽያ ቡና በአንፃራዊ መልኩ ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጓል። በተለይም ዘንድሮ በዋናው ቡድን በመስመር ተከላካይነት የተጫወተው ኃይሌ ገብረትንሳይ በቡድኑ ውስጥ ነፃ ሚና ተሰጥቶት ግሩ ተንቀሳቅሷል። በ24ኛው ደቂቃ ኃይሌ ከርቀት የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን ቢያልፍም ከጀርባ የነበረው ተከላካይ ያወጣበት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ ተመስገን ዘውዱ እና ገዛኸኝ ደሳለኝ ያደረጉት ሙከራ ተጠቃሽ ነበር። በሀዋሳ በኩል በ13ኛው ደቂቃ ቴዎድሮስ መሐመድ የመጀመሪያውን ግብ ሙከራ ሲያደርግ ተመስገን ታምራት እንዲሁም ያሬድ መሀመድ ያደረጉት የግብ ሙከራ የሚጠቀስ ነው። የእንቅስቃሴ ለውጥ ባልታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾች እርስ በርስ ሲጋጩ እና የዳኛን ውሳኔ ሲቃወሙ በተደጋጋሚ ተስተውሏል። የጎል ሙከራ ባልታየበት በዚህ አጋማሽም ጎል ሳይቆጠርበት ወደ መለያ ምቶች አምርተው በኢትዮጵያ ቡና ቡድን አምስቱንም ሲያስቆጥሩ ሀዋሳዎች አንድ በማምከናቸው ጨዋታው በቡና አሸናፊነት ተጠናቋል።
የዋንጫ ጨዋታው ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2010 ሲከናወን 5:00 ላይ ኢትዮጽያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ ይጫወታሉ። ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ደግሞ 03:00 ላይ ለደረጃ ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል።
ዘንድሮ እየተከናወኑ በሚገኙት የማጠቃለያ ውድድሮች በተለይም ከ20 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚስተዋለው የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ብዙ ሊሰራበት የሚገባ እንደሆነ በግልፅ የታየበት ነበር። ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ውድድሮቹ አላማቸውን እንዳይስቱ ከፍተኛ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።