የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኤርትራ ጋር በነሐሴ ወር አጋማሽ አስመራ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል።
ከወራት አሰልጣኝ አልባ ቆይታ በኋላ አብርሃም መብራቱን የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሁለቱን ሀገራት ወንድማማችነት ለማጠናከር በማሰብ አስመራ ከተማ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ባሳለፍነው ሳምንት ደብዳቤ የላከ ሲሆን በምላሹም የኤርትራ ብሔራዊ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄውን መቀበሏን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ በመላክ አሳውቃለች ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጳጉሜ ወር ከሴራሊዮን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ከማድረጉ አስቀድሞ ለማድረግ የታሰበው ይህ የወዳጅነት ጨዋታ ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ አስመራ ከተማ ለማድረግ የታሰበ ሲሆን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከሰሞኑን ከኳታር ወደ አአ ሲመለሱ ጨዋታው የሚደረግበት ቀን የሚወሰን ይሆናል። ፌዴሬሽኑም መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ለመፈፀም እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ሰምተናል።
በ1990 በተቀሰቀሰው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኑ ከኤርትራ ክለቦች እና ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገው የማያውቁ ሲሆን አሁን በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው ግንኙነት ወደ ሰላም በመመለሱ የኢትዮዽያ ክለቦች ከኤርትራ ክለቦች ጋር የእንጫወት ፍላጎት እያሳዩ ይገኛል። ፋሲል ከተማ ጥያቄ አቅርቦ ከኤርትራ እግርኳስ ፌዴሬሽን መልካም ምላሽ ሲያገኝ የትግራይ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮም በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ጨዋታዎች ለማድረግ ጥያቄ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።