የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ተጀምረዋል

ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ 6 ቡድኖችን ለመለየት የሚደረገው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ እና ኦሮሚያ አካዳሚ ሜዳ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል።

8:00 ላይ በኦሮሚያ ወጣቶች አካዳሚ ሜዳ ጎጃም ደብረማርቆስን የገጠመው ሺንሺቾ ከተማ  1-0 አሸንፏል። በ5ኛው ደቂቃ ብርሃኑ ኦርዲላ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣችው ኳስ ሺንሺቾን ቀዳሚ ሊያደርግ የሚያስችል አጋጣሚ ነበር። በሂደት ቅርስ የያዘው የደብረማርቆስ ቡድን ሙሉ ብልጫን በተጋጣሚያቸው ላይ ቢያሳዩም በፊት መስመር ስል አለመሆናቸው ግብ ከማስቆጠር አግዷቸዋል። በተለይም በ24ኛው ደቂቃ መሀመድ አብደላ ከግብ ጠባቂው ጋር  አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያባከናት ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበች አጋጣሚ ነበረች።

ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን በ64ኛው ደቂቃ አማካዩ ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ መስመር ወደጎል አክርሮ በመምታት የሺንሺቾ አሸናፊነት ያበሰረችውን ጎል አስቆጥሯል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ደብረማርቆሶች ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ ሙከራ ቢያደርጉም የሺንሺቾ የመከላከል አደረጃጀት ግቡን ሳያስደፍር ጨዋታው ለማጠናቀቅ ችሏል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የደብረ ማርቆስ ተጨዋቾች የዳኛውን ውሳኔ ሲቃወሙ ያታየ ሲሆን ደጋፊዎችም ቅሬታቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ ለመግለፅ ሲሞክሩ ተስተውሏል። የሺንሺቾ ደጋፊዎችም የዳኛውን ውሳኔ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲቃወሙ ታይቷል።

በቀጣይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቪን ከአራዳ ክፍለ ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ ቢሾፍቱ 1-0 አሸንፏል። በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመሩት ቢሾፍቱዎች በእንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በልጠው ቢንቀሳቀሱም በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫቸውን በግብ ሙከራዎች ሳያጅቡ ቀርተዋል። በ31ኛው ደቂቃ በአራዳ በኩል በቀኝ መስመር ዮናስ ባቤና ያደረግው ለግብ የቀረበ  ሙከራም በዚህ አጋማሽ የታየ ብቸኛ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

የተሻለ እንቅስቃሴ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በ75ኛው ደቂቃ በተጫዋቾች ተደርባ የተመለሰችውን ኳስ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ያሲን ጀማል አክርሮ በመምታት የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ብቸኛ የድል ጎል አስቆጥሯል። ከግቡ በኃላ አብዱልመጢፍ ሙዳል ሞክሮ የግቡን የግራ አግዳሚ ታካ የወጣችበት ሙከራ የአውቶሞቲቭን የጎል መጠን ልታሳድግ የምትችል የነበረች ሲሆን በጨዋታው 85ኛ ደቂቃ ላይ አራዳዎች የተጫዋች ተገቢነት ክስ አስይዘው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር  ጨዋታው በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በተመሳሳይ ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታድየም የተደረገው የወላይታ ሶዶ እና አሶሳ ከተማ ጨዋታ በወላይታ ሶዶ 2ለ1 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቀጥሎ የተከናወነው የሞጆ ከተማ እና የዳሞት ከተማ ጨዋታ በሞጆ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2010

8:00 ራያ አዘቡ ከትግራይ ውሃ ስራ (አበበ ቢቂላ)

10:00 ናኑ ሁሩቡ ከ ገላን ከተማ (አበበ ቢቂላ)

8:00 ቱሎ ቦሎ ከ አቃቂ ቃሊቲ (አካዳሚ)

10:00 አምባ ጊዮርጊስ ከ አርሲ ነገሌ (አካዳሚ)