በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም የተካሄደው ተጠባቂው የባህርዳር ከተማ እና የሽረ እንዳሥላሴ ጨዋታ 2-2 በሆነ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ባህርዳር ከተማም ወደ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ለማረጋገጥ ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚጠብቅ ይሆናል።
በርካታ ደጋፊዎች የታደሙበት የዕለቱ ጨዋታ ከተሰጠው ትኩረት አንፃር ኢንተርናሽናል ዳኞች የተመደቡለት ሲሆን በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት፣ ዳኛ ትግል ግዛው እና ክንዴ ሙሴ ደግሞ ረዳቶቹ ነበሩ።
ጨዋታው በሁለቱም በኩል ጎል ለማስተናገድ ብዙ ደቂቃዎች አልፈጁበትም። 3ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ልደቱ ለማ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠው ቅጣት ምት ሲሻማ ራሱ ልደቱ ለማ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ለውጦ ሽረን ቀዳሚ ያደረገ ቢሆንም የሽረ መሪነት መዝለቅ የቻለው ግን ለ3 ደቂቃዋች ብቻ ነበር። 7ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ግርማ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ፍቃዱ ወርቁ ወደግብነት ለውጦ ባህርዳርን አቻ አድርጓል። ከዚህ በኋላ ባህርዳር ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተለይም በ8ኛው ደቂቃ ዳንኤል ኃይሉ የሞከረው እንዲሁም በ15ኛው ደቂቃ ሙሉቀን ታሪኩ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ ሀፍቶም ያዳነበት የግብ ሙከራዎች በጣና ሞገዶቹ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ። 24ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ወርቁ አክርሮ የመታውን ኳስ በድጋሚ የሽሬ ግብ ጠባቂ ያዳነበት አጋጣሚም የሚነሳ ነው። በዚህ አጋማሽ ወደ ኋላ አፈግፍገው ሲጫወቱ የነበሩት ሽረዎች አልፎ አልፎ ከሚጥሏቸው ኳሶች በስተቀር አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ18ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ ከብሩክ ገብረዓብ የተሰጠውን ኳስ የሞከረበት አጋጣሚም ለግብ የቀረበ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በመጀመርያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የነበሩት ሽረዎች ሁለተኛው አጋማሽን በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩ ሲሆን ይህም ግብ እስከሚያስቆጥሩ ድረስ የዘለቀ ነበር። በ57ኛው ደቂቃ በግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ልደቱ ለማ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሮ በድጋሚ ሽረን መሪ አድርጓል። ከዚህች የልደቱ ሁለተኛ ግብ በኋላ ባህርዳር ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በተለይ ሙሉቀን በ69ኛው ደቂቃ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እንዲሁም ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግርማ ዳሲሳ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂውን አልፎ ከጀርባው የነበረው ተከላካይ ዘላለም በረከት ደርሶ ያዳነበት አስቆጪ የግብ እድሎች ነበሩ። በተጨማሪው ደቂቃ ላይ ፍቀረሚካኤል አለሙ በግርማ ደሲሳ አማካኝነት የተሻማውን ኳስ ወደ ግብነት ለውጦ ባህርዳርን አቻ አድርጓል። ሚኪያስ ግርማ በዛው ቅፅበት ራሱን ስቶ በመውደቁ ወደ ለህክምና ወደ ሆስፒታል ተልኮ ጨዋታውም በ2-2 አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ስፍራው በማቅናት የሚኪያስን የጤንነት ሁኔታ የተመለከትን ሲሆን ተጫዋቹ በመተንፈሻ አካሉ ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስበትም አሁን ግን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። ሆኖም የህክምና ክትትሉ በቅርበት እንዲቀጥል እዛው ሪፊት ቫሊ ሆስፒታል እንደሚያድር ታውቋል።
ቀጣይ ደረጃዎችን የመወሰን ኃይል በነበራቸው ሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ለገጣፎ ከ አዲስ አበባ እንዲሁም ቡራዩ ከ ሰበታ በተመሳሳይ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል። ሱሉልታ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት የሚያከብድ የ4-2 ሽንፈት በሜዳው በአማራ ውሃ የ4-2 ሽንፈት ሲገጥመው ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ መድንን 3-1 አሸንፏል። ደሴ እና ኢኮስኮ የ2-2 አቻ ውጤት ሲያስመዘግቡ ፌዴራል ፖሊስ ከ የካ የሚያደርጉት ጨዋታ ነገ በ4፡00 ሰዓት ላይ በኦሜድላ ሜዳ ይደረጋል።
በምድብ ለ ዛሬ አንድ የ24ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ተከናውኖ ወደ መቂ ያቀናው ሀላባ ከተማ 1-1 አቻ በመለያየት ከመሪዎቹ የነበረውን ልዩነት የማጥበብ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።