ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሽመልስ በቀለ በቅድመ ውድድር ዝግጅት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ክለቡ ፔትሮጀት ፋርኮንን 5-2 በረታበት ጨዋታ ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ሐት ትሪክ ሰርቷል።
የ2018/19 የውድድር ዘመንን በሐምሌ 24 የምትጀምረው ግብፅ የሊግ ውድድሯ ከመጀመሩ አስቀድሞ ክለቦቿ ከሳምንት በፊት ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸው ይታወቃል። ለግብፁ ክለብ ፔትሮጀት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በመጫወት ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አጥቂ ሽመልስ በቀለ ትላንት ምሽት በግብፅ ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን እየተሳተፈ ከሚገኘው ፋርኮን ክለብ ጋር ባደረገው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ላይ ፔትሮጀት 5-2 ሲረታ ላይ ሙሉ 90 ደቂቃ የተጫወተው ሽመልስ 3 ጎሎችን በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርቷል።
በ2017/18 የውድድር ዘመን ደካማ ጊዜ በማሳለፍ 12ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ፔትሮጀት በዘንድሮ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በርከት ያሉ ተጨዋቾችን ማስፈረም መቻሉ እየተነገረ ይገኛል። ከሽመልስ በቀለም በሚቀጥለው ዓመት ከክለቡ ጋር ቆይቶ የኮንትራት ዘመኑ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
በውድድር ዓመቱ አራት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው ሽመልስ በቀለ በቅርቡ በሚጀምረው የግብፅ ሊግ የውድድር ዘመን እንደሚያንፀባርቅ ሲጠበቅ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዻጉሜ 2 ቀን ከሴራሊዮን ጋር ለሚኖረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጥሪ ይደረግለታል ተብሎ ይጠበቃል።