ኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተጫዋቾችን የግሉ ለማድረግ ተስማምቷል

ኢትዮጵያ ቡና ከወዲሁ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ራሱን ማጠናከር የጀመረ ሲሆን ሁለት የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ሲደርስ ውላቸው ከተጠናቀቀ ዘጠኝ ያህል ተጨዋቾች ጋር ደግሞ ተለያይቷል።

በርካታ ተጫዋቾችን በመልቀቁ በክረምቱ የዝውውር መስኮት በስፋት እንደሚንቀሳቀስ የሚጠበቀው ኢትዮጵያ ቡና ሁለት የአርባምንጭ ከተማ የኋላ መስመር ተሰላፊዎችን በእጁ አስገብቷል። የመጀመሪያው ተጨዋች ከአርባምንጭ በፊት በደደቢት የምናውቀው የግራ መስመር ተከላካዩ ተካልኝ ደጀኔ ነው። ተካልኝ ስለዝውውሩ ያለውን አስተያየት ሲሰጥ ” በሚኖረኝ ጊዜ ሁሉ ለቡና ገበያ የአቅሜን የህል ማበርከት ፈልጌ እና ወስኜ ነው የመጣውት።  ደጋፊዎቹም ስበውኝ ቡናን ልቀላቀል ችያለው። ” ብሏል። ተጨዋቹ በርካታ ለውጦች ሲደረጉበት የቆየውን የኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ተከላካይ ቦታን በመደበኛነት ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንደሚሸፍን ይጠበቃል።

” ኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ክለብ ነው። እዚህ ክለብ ውስጥ ገብቼ የመጫወት ዕድል ማግኘቴ ለኔ ኩራት ነው። ክለቡ የብዙ ደጋፊዎች ባለቤትም ጭምር ነው። ከቡድኑ ጋር የተሻለ  ቆይታ እንደሚኖረንም እተማመናለሁ። ” በማለት ሀሳቡን የገለፀው ደግሞ ዘንድሮ ከፕሪምየር ሊጉ የወረደው አርባምንጭን ለቆ ወደ ቡናማዎቹ የመጣው ሌላኛው ተጨዋች ተመስገን ካስትሮ ነው። የፀጉሩን ቀለም ወደ ነጭ ቀይሮ ከርቀት የሚለየው ተመስገን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመሀል ተከላካይነት አዞዎቹን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በፊት አጥቂነት ሚናም እየተሰለፈ በመጫወት አምስት ግቦችን ከመረብ አገናኝቷል። የቀድሞው የሻሸመኔ ከተማ እና ሲዳማ ቡናው ተጫዋቾች በግሉ ጥሩ የሚባል የውድድር ዓመት ካሳለፈ በኋላ ቀጣይ ማረፊያውን በኢትዮጵያ ቡና አድርጓል፡፡

በተያያዘ ዜናም አምበሉ መስዑድ መሐመድን ጨምሮ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ አክሊሉ አያናው ፣ አለማየሁ ሙለታ ፣ ባፕቴስት ፋዬ ፣ አስቻለው ግርማ ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ ኤፍሬም ወንድወሰን እና ግብ ጠባቂው ሀሪሰን ሄሱ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የነበራቸው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ከክለቡ ጋር አብረው እንደማይቀጥሉ ተሰምቷል።