የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ መርሐ ግብር ከሴራሊዮን ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የሚያካሂድበትን ቦታ እና ቀን ወስኗል።
ካፍ የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎቹ ከጳጉሜ 2-5 ባሉት ቀናት እንደሚካሄድ አሳውቆ የነበረ ሲሆን ፌዴሬሽኑም ከሴራሊዮን የሚያደርገውን ጨዋታ እሁድ ጳጉሜ 4 ቀን 2010 በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታድየም 10:00 ላይ ለማድረግ እንደወሰነ ታውቋል።
ብሔራዊ ቡድኑ በ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታውን ሀዋሳ ላይ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ሲሸልስን 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል። ስታድየሙ ከዚህ ቀደምም የሴካፋ፣ የወዳጅነት፣ የማጣርያ እና የአፍሪካ የክለብ ውድድሮችን ማስተናገዱ ይታወቃል።
ባለፈው ሳምንት አብርሀም መብራቱን አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 5 ከጋና፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ ጋር መደልደሉ የሚታወስ ሲሆን በመጀመርያ ጨዋታው በጋና 5-0 በመሸነፉ የምድቡን ግርጌ ይዞ ይገኛል።