ሴካፋ 2018 | ታንዛንያ በድጋሚ ቻምፒዮን ስትሆን ኢትዮጵያ በ3ኛነት አጠናቃለች

በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 12 ጀምሮ ሲደረግ የቆየው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ዛሬ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 3ኛ ደረጃ ይዞ ጨርሷል።

ከሁሉም ቡድኖች ከፍተኛውን የቻምፒዮንነት እድል ይዘው ዛሬ 09:00 ላይ ታንዛንያን የገጠሙት ሉሲዎቹ 4-1 ተሸንፈው እድላቸውን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ29ኛው ደቂቃ መሠሉ አበራ ለመሀል ሜዳ ከተጠጋ ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም በቀጥታ በመምታት አስቆጥራ የመጀመርያውን አጋማሽ ኢትዮጵያ በመሪነት እንድታገድድ ረድታለች። ተከላካይዋ መሠሉ በተከታታይ 3 ጨዋታዎች ጎል ያስቆጠረች ሲሆን ሁለቱ ከቅጣት ምት የተገኙ ናቸው።

ሉሲዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተዳክመው ሲቀርቡ ታንዛንያዎች በተሟላ የማጥቃት ኃይል ኢትዮጵያን የመከላከል አደረጃጀት አፈራርሰውታል። ኢትዮጵያ የተከላካይ ቁጥር በመጨመር ወደ ሜዳ ብትገባም ገና ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ምዋናሀምሲ ዑማሪ ግብ ካስቆጠረች በኋለ ነገሮች ለታንዛንያ ቀላል ሆነዋል። በ58ኛው ደቂቃ በግሩም የመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ሚንጃ ዶኒሲያ አስቆጥራ ታንዛንያን ወደ መሪነት ስታሸጋግር ስቱማይ አብደላህ በ62ኛው ደቂቃ ሦስተኛውን አክላለች። መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ደግሞ ፋቱማ ሙስጠፋ የማሳረጊያውን አስቆጥራ ጨዋታው በታንዛንያ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ የ2016 ቻምፒዮኗ ታንዛንያ በ7 ነጥቦች በድጋሚ ቻምፒዮን ስትሆን ሁለሀኛ ደረጃ የመያዝ እድል የነበራት ሩዋንዳ በኬንያ በመሸነፏ እድሏን ሳትጠቀም ቀርታለች። በዚህም መሠረት ዩጋንዳ በ7 ነጥቦች በግብ ልዩነት ተበልጣ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ኢትዮጵያ በ6 ነጥቦች ሶስተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ ለተከታታይ ውድድሮች የነሀስ ሜዳልያ ባለቤት ሆናለች።