ወላይታ ድቻ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል

ከፕሪምየር ሊጉ ከመውረድ በመጨረሻው ጨዋታ የተረፈው ወላይታ ድቻ የ3 ተጫዋቾችን ፊርማ እንዳጠናቀቀ አስታውቋል።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሁሊሶ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ሳምሶን ቆልቻ፣ ታሪክ ጌትነት እና ኄኖክ ኢሳይያስ ለክለቡ ፈርመዋል።

ሳምሶን ቆልቻ በ2006 ወላይታ ድቻ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ሲሆን አንድ የውድድር ዓመትም ከክለቡ ጋር በሊጉ ማሳለፍ ችሎ ነበር። በ2008 በደሴ ከተማ፣ በ2009 በሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቻምፒዮኑ ጅማ አባ ጅፋር አሳልፎ ወደ ቀድሞ ክለቡ በመመለስ በ2 ዓመት ኮንትራት ተቀላቅሏል።

ኄኖክ ኢሳይያስ በአንድ ዓመት ኮንትራት ድቻን ተቀላቅሏል። የቀድሞው የደደቢት አማካይ ባለፈው የውድድር ዓመት መጀመርያ ወደ ሽረ እንዳሥላሴ ካመራ በኋላ በግማሽ ዓመት ወደ ጅማ አባ ቡና አቅንቶ ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ የተጠናቀቀውን ዓመት በሌላው የጅማ ክለብ ጅማ አባ ጅፋር አሳልፏል። በተለያዩ ሚናዎች የሚጫወተው ኄኖክ ለአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ አማራጮች እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ሌላው ለቡድኑ የፈረመው ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ነው። ታሪክ በ2004 ወደ ዋናው ቡድን ካደገ ወዲህ የተጫዋችነት ዘመኑን በደደቢት ያሳለፈ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድንም በተደጋጋሚ የመጠራት እድል አግኝቷል። ግብ ጠባቂው በድቻ የአንድ ዓመት ኮንትራት ተፈራርሟል።

ክለቡ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ ኮንትራታቸው የተገባደዱ 5 ተጫዋቾችንም ውል አድሷል። አብዱልሰመድ ዓሊ፣ ያሬድ ዳዊት፣ ሙባረክ ሽኩር፣ ጸጋዬ ብርሀኑ እና ውብሸት ዓለማየሁ ውላቸው የታደሰላቸው ተጫዋቾች ናቸው።

የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ባለፈው ዓመት የተከሰቱ የዝውውር ስህተቶችን ላለመድገም ተጠንቅቀው በዝውውር መስኮቱ እንደሚሳተፉና ተጨማሪ ተጫዋቾችን በቀጣይ ጊዜያት ለማስፈረም እንደሚንቀሳቀሱ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።