የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በክልል እና በአዲስ አበባ ሲደረጉ መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድንን የገጠመው ባህር ዳር ከተማ 2-1 ጨዋታውን በማሸነፍ ገና ሶስት ቀሪ ጨዋታዎች እየቀሩት በቀጣይ አመት በፕሪምየር ሊጉ ላይ መሳተፉን አረጋግጧል።
4 ሰዓት ላይ በተከናወነው ጨዋታ ለተጋባዦቹ ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያደርጉትን ጉዞ ከወዲው የሚያረጋግጡበት ለባለሜዳዎቹ ደግሞ ደረጃቸውን ከፍ የሚያደርጉበት ጨዋታ እንደመሆኑ በጉጉት ተጠብቆ የነበረ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ባህርዳር ከተማ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ኢትዮጵያ መድን ተሽለው ተንቀሳቅሰዋል።የሜዳው ውሃ መያዝ እና ጭቃ መሆን ጨዋታውን ያቀዘቅዘዋል ተብሎ የተፈራ ቢሆንም በሜዳው በተገኙ ደጋፎዎች ሞቅ ብሎ ጨዋታው ተጀምሯል።
ጨዋታው እንደተጀመረ ባህርዳሮች በሙሉቀን ታሪኩ አማካኝነት የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ከጨዋታው ገና በጊዜ ጎል ማገኘት እንደፈለጉ በማሳየት ተጭነው ለመጫወት ሲጥሩ ታይቷል።በ12ኛው ደቂቃም በእለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግርማ ዲሳሳ ከግራ መስመር ለፍቃዱ ወርቁ ያሻገረለትን ኳስ ፍቃዱ ኳሷን ሳይጠቀምባት ወደ ላይ ወጣች እንጂ ሌላ በጊዜ የተገኘ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበረ። ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ መድኖች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡ ሲሆን በ14ኛው ደቂቃም የመጀመረከያ ሙከራ አድርገዋል።ሰኢድ ኑሩ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን ቋሚ ታካ የወጣች ኳስ ስትሆን ቡድኑም ከዚች ሙከራ በኃላ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል ለመድረስ ኳሶችን አደራጅቶ ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል።የጣና ሞገዶቹ ከዚህም በፊት በሚታወቁበት ኳሶችን ወደ መስመር በማውጣት እና ወደ መሃል በማሻማት ግብ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረቶችን በማድረግ በ22ኛ ደቂቃ ሙሉቀን ከግርማ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቶ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ባህርዳሮች አፈግፍገው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን ይህ ደግሞ ለተጋጣሚያቸው የ መጫወቻ ሜዳ እንዲያገኝ በማድረጉ ጫናዎች ሲሰነዘርባቸው ታይቷል። መድኖች ይህንን ክፍተት በመጠቀም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ መድረስ የቻሉ ሲሆን በ38 እና 43ኛ ደቂቃም በአብዱላዚዝ አማካኝነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ሳያስቆጥሩ እየተመሩ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው የመጡት ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ አጥቂ በማስገባት እና አጨዋወታቸውን በመቀየር ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን በረጅም ኳሶችን እና በተሻጋሪ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በ48 እና በ51ኛ ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ታምሩ ባልቻ ከቅጣት ምት እና ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ኢላማዋን ስታ ወደ ውጪ ወታለች። ጥረታቸውን የቀጠሉት መድኖች በ61ኛው ደቂቃ በታምሩ ባልቻ የግምባር ኳስ የአቻነት ግብ ሲያገኙ ከግቧ መቆጠር በኃላ ጨዋታው እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ ፉክክሩ ቀጥሏል። አቻነታቸውን ከአምስት ደቂቃ በላይ ማስጠበቅ ያልቻሉት መድኖች በ66ኛው ደቂቃ የመጀመሪያው ጎል አመቻችቶ ባቀበለው ግርማ ዲሳሳ ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸው በድጋሚ የተመሩ ሲሆን ግርማ ኳሷን ያስቆጠረበት መንገድ ግን በሜዳው ባሉ ተመልካቾች አድናቆጥ አስችሮታል።
በተመሳሰይ በ75ኛው ደቂቃም ግርማ ሌላ የቡድኑን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ ሊያደርግ የሚችልበትን ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቶ ኳሷን በውስጥ እግሬ እመታለው ብሎ ሳይጠቀምበት የቀረው አስቆጪ እድል ነበር። ውጤታቸውን ለማስጠበቅ በሚመስል ሁኔታ ሶስቱንም የፊት አጥቂዎች አስወጥተው የአማካኝ እና የተከላካይ መስመር ተጨዋች ያስገቡት ባህርዳሮች የመሃል መስመር ተጨዋቹን ዳንኤልን እና ተቀይሮ የገባው ዳግምን ብቻ አልፎ አልፎ ወደ ፊት እንዲሄዱ በማድረግ በጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ውጤቱን ለማስጠበቅ ሞክሯል። የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ሰዓት መድኖች ሁለት የመዓዘን ምቶችን አግኝተው የነበረ ሲሆን አጋጣሚዎቹን ግን ሳይጠቀሙበት ተሸንፈው ወተዋል።
ባህርዳር ከተማ ድሉን ተከትሎ በ61 ነጥቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። በ1973 የተመሰረተው ባህርዳር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ሲያረጋግጥ በ2000 ከተሳተፈው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በኋላ ሁለተኛው የባህርዳር ቡድን ሆኗል።
በሌሎች የምድብ ሀ ጨዋታዎች ሽረ እንዳሥላሴ ሱሉልታን ያስተናገደበት ጨዋታ በሱሉልታ አለመገኘት ምክንያት በፎርፌ አሸንፎ በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ ሲቃረብ አአ ከተማ ከቡራዩ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ ከ ደሴ ከተማ በተመሳሳይ 1-1 አቻ ተለያይተዋል። አክሱምከ ለገጣፎ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሲለያዩ ኢኮስኮ ነቀምት ከተማን 1-0 አሸንፏል።
በምድብ ለ ሀላባ ከተማ የ25ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታውን ከዲላ ከተማ ጋር አድርጎ 3-0 በማሸነፍ የነጥብ ድምሩን 47 አድርሶ ከመሪው ደቡብ ፖሊስ የነበረውን ርቀት ወደ 3 ማጥበብ ችሏል።