ጅማ አባጅፋርን የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ወደ መቐለ ከተማ አምርተዋል፡፡
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አዲስ አዳጊው ጅማ አባጅፋርን ከአሰልጣኝ መኮንን ገ/ዮሀንስ በመረከብ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በማድረግ አመቱን ያጠናቀቁት አሰልጣኝ ገብረመድህን ከጅማ አባጅፋር ጋር ሐምሌ 20 ከክለቡ ጋር የነበራቸው ውል የተጠናቀቀ ሲሆን ላለፉት ሳምንታት ስማቸው በስፋት ሲያያዝባቸው የነበረው መቐለ ከተማን መቀላቀላቀላቸው እርግጥ ሆኗል።
አሰልጣኝ ገብረመድህንን የለቀቀው ጅማ አባጅፋር አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር አራት አሰልጣኞች እያወዳደረ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ይጠቁማል። አሰልጣኝ ገብረመድህንን በአንድ ዓመት ውል ወደ ክለቡ የቀላቀለው መቐለ በአንፃሩ በቀጣዩ ሳምንት ስለ አሰልጣኙ ቅጥር በይፋ እንደሚያሳውቅም ይጠበቃል።
የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ኮከብ ገብረመድህን ኃይሌ በአሁኑ ወቅት በሊጉ እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞች አንጋፋው ሲሆኑ በሊጉ ከ1993 ጀምሮ በትራንስ ኢትዮጵያ፣ ባንኮች፣ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ክለቦች አሳልፈዋል።