ሲዳማ ቡና የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ውል ሲያድስ የአጥቂው አዲስ ግደይንም ውል አራዝሟል፡፡
የአሰልጣኝ ዓለማየሁ አባይነህን መልቀቅ ተከትሎ በምክትል አሰልጣኝነት ሲያገለግል የነበረው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በክለቡ ያለፉትን አራት ወራት በክለቡ ለመቆየት ተስማምቶ ክለቡን ከወራጅነት ስጋት ተላቆ በሊጉ መቆየት አንዲችል መታደግ ችሏል ፡፡ ሲዳማ ቡና ለቀጣዩ የውድድር ዘመን በአዲስ አሰልጣኝ ይቀርባል ተብሎ ቢታሰብም ክለቡ የሁለት ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት ለአሰልጣኙ በመስጠት በክለቡ ማቆየት ችሏል፡፡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን ያደረገው አሰልጣኙ የተሻለ ጊዜን ከክለቡ ጋር ለማሳካት ማሰቡን ገልጿል “በቀጣዩ አመት ተፎካካሪ ቡድን መስራት ፈልጋሉ የተሰጠኝ ትልቅ ሀላፊነት ነው ይህን ደግሞ ለማድረግ በሚገባ ራሴን ለማዘጋጀት እና የተሰጠኝን እድል በአግባቡ ለመጠቀም አስባለሁ” ሲል ተናግሯል፡፡
በተጫዋችነት ዘመኑ በአማካይነት የሚታወቀው በሲዳማ ቡና የቡድኑ አምበል በመሆን ተጫውቷል። 2007 ላይ እግር ኳስን ካቆመ በኃላ ደግሞ የሲዳማ ቡና ከ17 አመት በታች አሰልጣኝ፣ በዋናው ቡድን ረዳት አሰልጣኝ እና ዋና አሰልጣኝም በመሆን ሰርቷል ፡፡
በተያያዘም ክለቡ የአዲስ ግደይን ውል ማራዘሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጿል፡፡ በክለቡ ያለፉትን ሶስት አመታት ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ በስፋት ከጅማ አባጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስሙ ሲነሳ የነበረ ቢሆንም በዛው ሲዳማ ቡና ለአንድ ዓመት መቆየቱ ተረጋግጧል። በተጨማሪነትም ክለቡ በቀጣዩ ቀናት አዳዲስ እና የነባር ተጫዋቾች ውል ለማራዘም በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጭምር ሰምተናል፡፡