ዋልያዎቹ ቀጣይ የማጣርያ ጨዋታቸውን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያደርጋሉ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሩስያ የ2018 አለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የሚያደርገው የመልስ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድየም እንደሚደረግ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ከቦትስዋና ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ በመጪው መስከረም 19 የሚያደርግ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ባስታወቀው መሰረት የቦትስዋና እግርኳስ ማህበር ሃገሪቱ የምታከብረውን የነፃነት በአል አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ግብዣ ልኳል፡፡ ፌዴሬሽኑም ጥያቄውን በመቀበሉ ከ16 ቀናት በኋላ በጋቦሮኒ የወዳጅነት ጨዋታው ይደረጋል፡፡

ቦትስዋና እና ኢትዮጵያ በ2014 የአለም ዋንጫ ማጣርያ በአንድ ምድብ ውስጥ የነበረች ሲሆን ጋቦሮኒ ላይ 2-1 አዲስ አበባ ላይ ደግሞ 1-0 ማሸነፋችን የሚታወስ ነው፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ከወዳጅነት ጨዋታው በኋላ ለሚጠብቁት የማጣርያ ጨዋታዎች ተሰባስቦ ዝግጅት እንደሚጀመርም ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከ1 ሳምንት በኋላ (ከቦትስዋና ጨዋታ ቀደም ብሎ) ተጫዋቾችን መርጠው በአዲስ አበባ ስታድየም ዝግጅት የሚጀመሩ ሲሆን ከጋቦሮኒ መልስም ዝግጅታቸውን በአዲስ አበባ ስታድየም ይቀጥላሉ፡፡

ፌዴሬሽኑ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የሚያደርገው የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በባህርዳር ስታድየም ሳይሆን በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያደርግ በመሆኑ ዝግጅቱም አዲስ አበባ ላይ ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የለፉትን 2 ተከታታይ የሜዳውን ጨዋታዎች በባህርዳር ስተድየም ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

የብሄራዊ ቡድናችን ቀጣይ ጨዋታዎች መርሃ ግብር የሚከተለው ነው፡-

መስከረም 19 – ከቦትስዋና ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ

መስከረም 27 – ከ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ (በ12 ዲ ጁሊሆ ስታድየም)

መስከረም 30 – ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር የአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ ( በአዲስ አበባ ስታድየም )

ከጥቅምት 5-7 ባሉት ቀናት – ከቡሩንዲ ጋር የቻን ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ( ከሜዳ ውጪ)

ከጥቅምት 12-14 ባሉት ቀናት – ከቡሩንዲ ጋር የቻን ማጣርያ የመልስ ጨዋታ (በሜዳው)

ያጋሩ