የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰባት ወራት ቆይታ በኃላ አሰልጣኝ ማግኘቱ ከዚህ ቀደም መነገሩ የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ አሰልጣኙ እና የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በተገኙበት በካፒታል ሆቴል እና ስፓ ይፋዊ የስራ ስምምነት እና የፊርማ ስነስርዓት ተከናውኗል።
ከታህሳስ 19 ጀምሮ ያለ አሰልጣኝ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን በይፋ መቅጠሩን ፌደሬሽኑ የተገለፀ ሲሆን አሰልጣኙም ከፊርማቸው በኃላ ከጋዜጠኞች በቀረበላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሾችን ሰጥተዋል።
55 ደቂቃዎችን በፈጀው ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ስለ ሁለቱ አካላት ስምምነት ተብራርቶ የተነገረ ሲሆን በአጠቃላይ ስለቅጥሩ ሁኔታ ፣ ስለ ብሔራዊ ብድኑ አሰልጣኝ ኃላፊነት እና ስለ ቀጣይ አመት ዕቅዶች ገለፃ ተደርጓል። መግለጫው የተጀመረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት በሆኑት አቶ ኢሳያስ ጂራ ንግግር ሲሆን ፕሬዝዳንቱም ረጅም ጊዜ ብሔራዊ ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ መቆየቱ ስህተት መሆኑን በመግለፅ አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ወደ ቦታው ከመጣ በኃላ ለብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ የቤት ስራዎችን በመስጠት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረው ነገሮች በፍጥነት እንዲከናወኑ መጣሩንም አስረድተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ስለ አሰልጣኝ ቅጥሩ እና የውሉ ጉዳይ ላይ በመቀጠል በሰጡት ማብራሪያ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ለሁለት አመት ከዋሊያዎቹ ጋር እንዲቆይ መስማማታቸውን እና የትራንስፖርት እንዲሁም የስልክ ወጪዎችን ሳይጨምር በወር የተጣራ 125 ሺህ እንደሚከፈላቸው ገልፀዋል። አቶ ኢሳያስ ከአሰልጣኙ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች እና ግቦች ሁለት መሆናቸውን በመግለፅ ለ2020 የአፍሪካ ሀገራት ሻምፕዮና (ቻን) ጠንካራ እና ተፎካካሪ ቡድንን ለመገንባት እና ከተቻለ ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ (ብሔራዊ ቡድኑ የማለፍ ዕድል ስላለው) እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን ነገር ግን ለ2019 የካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑ የማያልፍ ቢሆን እንኳን አሰልጣኙን እንደማያሰናብቱት ገልፀዋል። ይህን ሀሳባቸውን ሲያስረዱም “በኛ በኩል አሰልጣኙ በፈለገበት አይነት ሁኔትል ቡድኑን እንዲገነባ ነፃነት ሰጥተነዋል። አሰልጣኙ በዚህ ሁለት አመት ጠንካራ እና ተፎካካሪ ቡድን እንዲሰራ እንፈልጋለን። በ2020 የቻን ውድድር ላይ ጥሩ ቡድን እንዲኖረን እንፈልጋለን። ነገር ግን በ2019 የሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ካላለፍን አሰልጣኙ ላይ ውሳኔዎችን አናስተላልፍም። ማሰብ ያለብን ቡሔራዊ ቡድናችንን ለረጅም ጊዜ የመገንባቱ እና ቦታው እንዲረጋጋ የማድረጉ ጉዳይ ላይ ነው።” ብለዋል። የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱን አሰልጣኙ በራሱ መርጦ ለፌደሬሽኑ እንደሚያስታውቅ የገለፁት አቶ ኢሳያስ አሰልጣኙ ዘንድሮ ሀገር ውስጥ ያልነበሩ በመሆኑ ሁሉም እግር ኳሱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ሊረዱዋቸው እንደሚገባም ጨምረው አሳስበዋል።
ከፕሬዘዳንቱ ንግግር በመቀጠል የፊርማ ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን ከስነስርዓቱ በኃላ አሰልጣኙ ስለ ተለያዩ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል። “ያለኝን አቅም እና እውቀት ከግንዛቤ በማስገባት ሀገሬን እንዳገለግል ጥሪ ስለቀረበልኝ አመሰግናለው።” ብለው ንግግራቸውን የጀመሩት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ሀላፊነቱ ከባድ እንደሆነ በማንሳት የሳቸው ጥረት እና ልፋት ብቻውን ቡድኑን ወደ ሚፈለገው ደረጃ እንደማያደርሰው ተናግረዋል። “እውነት ለመናገር ብሔራዊ ቡድኑን ወደ ስኬት ለማምጥት የኔ ልፋት እና ጥረት በቂ አይደለም የሁሉም የስፖርት ቤተሰብ እና ባለ ድርሻ አካላት እገዛ እና ትብብር የጠበቃል።” ብለዋል።
በመቀጠል ስለ ረዳት አሰልጣኝን የሚመርጡበት መንገድ እና ስለ ስብስቡ የተናገሩት ኢንስትራክተሩ ምክትል አሰልጣኝ የሚመርጡት ልምድን እና አሰልጣኙ ለሊጉ ያለውን ቅርበት ታሳቢ አድርገው እንደሆነ ያስረዱ ሲሆን ወጣት እና ተግባቢ ቢሆን ደግሞ የበለጠ እንደሚወዱ ተናግረዋል።
ከተለያዩ የሚድያ አካላት ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ የሰጡት ሁለቱ አካላት ያልጠሩ እና በደንብ መገለፅ አለባቸው በተባሉም ሃሳቦች ላይ ገለፃ አድርገዋል። ስኬት ባይመጣ እንኳን አሰልጣኙን እንደማያሰናብቱ የተጠየቁት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት “እኛ የምንፈልገው ጠንካራ እና ጥሩ ብሔራዊ ቡድን እንዲገነባልን ነው ይህ ማለት ግን ውጤት አንፈልግም ማለት አይደለም። በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ገና ቀሪ 5 ጨዋታዎች ስለሚቀሩ ዕድል አለን። ስለዚህ ጥሩ ነገር እንዲመጣ እንፈልጋለን። ነገር ግን ለአጭር ጊዜ ስኬት ሳይሆን ለቀጥይ ወጥ እና አስተማማኝ ብሔራዊ ቡድንን ስለምንፈልግ አሰልጣኙ ተረጋግቶ እንዲሰራ ነው የምናደርገው” ብለዋል።
በቀጥይ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የጀመሩት አዲሱ አሰልጣኝ በርከት ባሉ ነጥቦችን አብራርተዋል። ከዚህ ውስጥ ስለ አሰልጣኝ አባላትን ቁጥር ስለማስፋት እና ዘመናዊ የስልጠና መንገድን ስለመከተል የተጠየቁ ሲሆን የሚከተለውን ምላሽ ሰተዋል። ” በውጪ ሀገራት እንደምናየው በቁጥር ብዙ የሆኑ የአሰልጣኞች ስብስብ አላቸው። ነገር ግን ይሄ በኛ ሀገር አልተለመደም። እኔ ግን የተደራጀ የአሰልጣኝ ቡድን ለመስራት ከፌደሬሽኑ ጋር ተነጋግሬ ጨርሻለው። በአቅማችን ከምክትል አሰልጣኝ እና ከግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በተጨማሪ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ፣ የስነ ምግብ ባለሙያ ፣ የቪዲዮ አናሊሲስ እና የሚዲያ ኦፊሰር በማምጣት ቡድኑን ለማጠናከር ከብሔራዊ ፌደሬሽኑ ጋር ተስማስማምተናል። ይህ ደግሞ ስራዎችን ያቀሉልናል ብለን እናስባለን።” ብለዋል። ስለ ተጨዋች ምርጫ እና ስለ ዝግጅታቸው ለተሰነዘሩ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ድግሞ ” ዝግጅታችንን ነሀሴ 1 በሃዋሳ እንጀምራለን ብለን እናስባለን የምክትል አሰልጣኞች እና ተያያዥ ጉዳዮችን ደግሞ በተመለከተ በሶስት ቀን ውስጥ ለፌደሬሽኑ በማሳወቅ ቶሎ ወደ ስራ እንገባለን ብለን እናስባለን። በመቀጠል ከአሰልጣኝ ቡድን አባላቶቼ ጋር ሆነን በየቦታው ሶስት ሶስት ተጨዋቾችን እንመርጣለን። ከዛ በዝግጅት ጊዜያችን ከመረጥናቸው ሶስት ሶስት ተጨዋቾ አንድ አንዱን በመቀነስ በየቦታው ሁለት ሁለት ተጨዋቾችን በማድረግ በአጠቃላይ 23 ተጨዋቾችን እንመርጣለን ብለን አቅደናል።” በማለት ነበር። በመጨረሻም አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ብቻ ተጨዋች እንደማይመርጡ በመናገር ለብሄራዊ ቡድን ብቁ የሆኑ እና ጥሩ ተጨዋቾችን ከየትኛውም ቦታ ቢያገኙ ወደ ስብስባቸው እንደሚቀላቅሉ አሳስበው ገልፀዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ማብቂያ ላይ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በተከሰተው እና የህዳሴው ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ በነበሩት ኢ/ር ስመኘው በቀለ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በመግለፅ ለቤተሰቦቻቸው ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን የተመኙ ሲሆን በስፍራው የነበሩ ሰዎችም ለኢ/ሩ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲያደርጉ በመጠየቅ ስነ-ስርዓቱን አጠናቀዋል።