ከገብረመድህን ኃይሌ ጋር የተለያየው ጅማ አባ ጅፋር ዮሀንስ ሳህሌን ቀጣዩ የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መርጧል። የ2010 የሊግ ቻምፒዮኖቹ የገብረመድህንን ቦታ ለመተካት ዮሀንስን ጨምሮ ፋሲል ተካልኝ እና ብርሀኔ ገብረግዚአብሔርን ያወዳደረ ሲሆን በመጨረሻም ወደ ዮሀንስ ሳህሌ በማጋደል ከአሰልጣኙ ጋር ከስምምነት መድረስ ችሏል። ዛሬ ከሰዓትም በይፋ ኮንትራት ይፈራረማሉ ተብሏል።
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ወዲህ በ2006 ደደቢትን ሲያሰለጥኑ በ2007 ብሔራዊ ቡድኑን ተረክበው እስከ 2008 አጋማሽ ቆይታ በማድረግ በድጋሚ ወደ ደደቢት ተመልሰው ከአጭር ጊዜ የቆየ ቆይታ በኋላ ለቀዋል። የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ደግሞ አዲስ አዳጊው መቐለ ከተማን ተረክበው 4ኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል።
ጅማ ዋና አሰልጣኙን ወደ መቐለ ሲሸኝ በምትኩ የመቐለ አሰልጣኝ የነበሩትን ወደ ክለቡ ለማምጣት ተስማምቷል። በርካታ ተጫዋቾችን እያጣ የሚገኘው ክለቡም ከዛሬ ጀምሮ የአዳዲስ ተጫዋቾች ፊርማ እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል።
በተያያዘ ዜና አቶ ኢሳይያስ ጂራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ስራ አስኪያጅ ሳይቀጥር ቆይቶ የነበረው ጅማ አቶ እስከዳር ዳምጠውን ቀጥሯል። ግለሰቡ በድሬዳዋ ከተማ ስራ አስኪያጅነት እስከ ውድድር ዘመኑ አጋማሽ ድረስ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።