በውድድር አመቱ መጀመሪያ ሲዳማ ቡናን ለሁለት ዓመታት ተቀላቅሎ የነበረው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ የዓንድ አመት ኮንትራት እየቀረው ከክለቡ ጋር ተለያይቷል፡፡
የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ ያለፉትን አራት ወራት ከዘንድሮው ክለቡ ሲዳማ ቡና ጋር በገባባት ሰጣ ገባ ምክንያት ከክለቡ እንደራቀ እና ለመለያየትም እንደበቃ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ አስረድቷል። “እኔ ወደ ክለቡ ሳመራ በነፃነት ለመጫወት አስቤ ነበር። ነገር ግን በጊዜ ሂደት በክለቡ ውስጥ አንዳንድ ተጫዋቾች የሚያሳድሩብኝ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደፈለኩ አቅሜን አውጥቼ መጫወት እንዳልችል አድርጎኛል። የክለቡ ስራ አስኪያጅም በምፈልገው ልክ ማግኘት ያለብኝን ነገር እንዳላገኝ አድርገውኛል። እንደ አንድ ተጫዋች ማግኘት ያለብኝ ነገሮች ስለቀሩ እና መግባባትም ስላልቻልኩ ለፌድሬሽኑ አመልክቼ ፌድሬሽኑ ለኔ ተገቢውን ምላሽ ሰጥቶኛል። ሆኖም እስካሁን የአንድ ወር ደሞዜን ማግኘት አልቻልኩም። ነገር ግን ውሉ ወደ አንድ አመት ዝቅ እንዲል ተስማምተን ከክለቡ ጋር በቀጣይ አመት የሚኖረኝ አንድ አመት እንዲቀር ተወስኖልኛል። በዚህም መሰረት ነገ ከክለቡ መልቀቂያዬን ወስጄ ወደ ሌላ ክለብ ለመሄድ ተዘጋጅቻሁ።” ብሏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሰጡት የሲዳማ ቡና ፕሬዝዳንት አቶ መንግስቱ ሳሳሞ በበኩላቸው ጉዳዩን አስመልክተው ሀሳባቸውን ሲያስረዱ “ተጨዋቹ ከክለቡ እና ከተጨዋቾች ጋር መግባባት ባለቻሉ ለጊዜው ከክለቡ እንዲርቅ ውሳኔ ላይ ደርሰን ነበር። አሁን ደግሞ ተጨዋቹ ከፌዴሬሽን የውሳኔ ደብዳቤ ይዞ በመምጣቱ ነገ መልቀቂያውን የምንሰጠው ይሆናል።” በማለት ነበር።
በ2006 ወደ ወላይታ ድቻ አምርቶ እስከ 2008 ከቆየ በኋላ ወደ መከላከያ በማቅናት ሁለት ዓመታትን አሳልፎ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው የፊት አጥቂ ከክለቡ ጋር ያለው ቆይታ በዚህ ሁኔታ የተጠናቀቀ ሲሆን በቀጣይ ወደ ሌላ የፕሪምየር ሊጉ ክለብ እንደሚያመራ ይጠበቃል።