የ2017/18 የአልባኒያ ሱፐርሊጋ እና የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ያሸነፈው ኬኤፍ ስከንደርቡ በአውሮፓ የእግርኳስ ማህበር የተጣለበት የ10 ዓመት እገዳ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ተከትሎ ክለቡ በዩኤፋ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ላይ እየተሳተፈ አይገኝም፡፡
በኮርሲው ክለብ ፋንታ የውድድር ዓመቱን በሁለተኝነት የጨረሰው ኬኤፍ ኩክሲ በቻምፒየንስ ሊጉ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ በክለቡ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ የሁለት ዓመት ውል ቢኖረውም የስከንደርቡ እጣ ፋንታ ብዙዎቹን ተጨዋቾች ወደ መውጫው በር እንዲመለከቱ እያደረጋቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የቢንያም የስከንደርቡ ቆይታ አጠያያቂ አድርጎታል፡፡ የዓለምአቀፉ የስፖርት ገላጋዮች ፍርድ ቤት (ካስ) የስከንደርቡን የ10 ዓመት እገዳ ዳግም እያጤነው ቢሆንም ቅጣቱ የመቅለሉ ወይንም የመነሳት እድሉ እጅግ በጣም የጠበበ ነው፡፡
ዩኤፋ በስከንደርቡ ላይ የጨዋታ ውጤቶችን ከማጭበርበር እና በህገወጥ መንገድ ከጨዋታ አወራራጅ ድርጅቶች ጋር በመተባባር ጨዋታዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ወደ ካዝናው አስገብቷል በሚል የሚወነጅል ሲሆን ለዚህም በቂ ማስረጃዎች አሉኝ በማለት ነበር በዓይነቱ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለ10 ዓመታት ከማንኛውንም ዓይነት የአውሮፓ የክለብ ውድድሮች የኮርሲውን ክለብ ያገደው እና በተጨማሪም የ1.1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የቀጣው፡፡ ዩኤፋ እንደማስረጃነት ከ2010 ጀምሮ ስከንደርቡ 53 የሚጠጉ በአውሮፓ የክለቦች ውድድሮች፣ የአልባኒያ ሱፐርሊጋ ጨዋታዎች እና የወዳጅነት ግጥሚያዎች ላይ የጨዋታ ማጭበርበር እንደፈፀመ ይገልፃል፡፡
የክለቡ ፕሬዝደንት አድሪያን ታካ በዚህ ወንጀላ አይስማሙም፡፡ ታካ እንደሚሉት ዩኤፋ የሚተገብረው Betting Fraud Detection System (BFDS) ለማስተዋወቅ “በትንሽ ሃገር እና በትንሽ በጀት በሚንቀሳቀስ ክለብ ላይ የሚተገብረው ነው” ይላሉ፡፡ ዩኤፋ በአንፃሩ “ክለቡ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የጨዋታ ውጤቶች ለውርርድ እንዲመቹ አድርጎ አስቀይሯል” ይላል፡፡
ይህ ከባድ ወንጀል ክለቡን በፋይናንስ ከማዳከሙ ባሻገር በአውሮፓ ውድድሮች ተሳትፎ የሚያገኘውን ዳጎስ ያለ ገቢ (ስከንደርቡ በዮሮፓ ሊግ ውድድር ምድብ ውስጥ የገባ ብቸኛው የአልባኒያ ክለብ ነው) ያሳጣዋል፡፡ ይህም ባለፉት 8 ዓመታት በአልባኒያ የነገሰውን ክለብ ወንበር የሚነቀንቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው የክለቡ ቁልፍ ተጨዋቾች ከወዲሁ ወደ ሌሎች የተሻሉ ክለቦች እና ሃገራት ማምራት የጀመሩት፡፡ እገዳው ከፀና ደግሞ ይህ የተጨዋቾች ፍልሰት ይበልጥ የሚጠናከር ይሆናል፡፡ የቢያንም ቆይታም ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ይጠበቃል፡፡ ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ በግንቦት ወር በመጣ ወቅትም ቢኒያንም ስለቀጣይ ቆይታው ወደ አልባኒያ ከተመለሰ በኃላ ከወኪሎቹ ጋር እንደሚወያይ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቆ ነበር፡፡