የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። በዛሬው የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ውሎም ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉ 4 ክለቦች ታውቀዋል።
ጠዋት 03:00 ላይ የተጀመረው የእለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በአርሲ ነጌሌ እና ወላይታ ሶዶ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ግብ ሳይቆጠርበት በመለያ ምቶች አርሲ ነጌሌ አሸናፊ መሆን ችሏል። ንጋት ላይ በጣለው ዝናብ ምክንያት ውሀ ያዘለው ሜዳ ለጨዋታ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን በተለይ ኳስ በተደጋጋሚ አቅጣጫ ለተከላካዮች ራስ ምታት ሲሆን ተስተውሏል። በ12ኛው ደቂቃ በዚሁ ሒደት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ አብዲስ ጀማል ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ አርሲን ቀዳሚ ማድረግ በቻለ ነበር። ከ2 ደቂቃዎች በኋላ ፍስሀ ሮባ ከቀኝ መስመር በግራው አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያወጣበት ሙከራም በአርሲዎች በኩል ሌላው የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። በሶዶ በኩል ደግሞ አሸናፊ ማለ በ39ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከነውና በ44ኛው ደቂቃ ያሬድ ደርዘ ከቅጣት ምት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
እጅግ የተቀዛቀዘና ሙከራዎች ያልታዩበት የሁለተኛው አጋማሽ አርሲዎች ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች ጎል ለማስቆጠር ሲጥሩ በሶዶ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ አልታየም። ጨዋታው ያለጎል መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርተው አርሲ ነጌሌ 4-3 አሸንፎ ወደ ከፍተኛ ሊግ መግባቱን አረጋግጧል። በ2009 ከከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ወደ አንደኛ ሊግ የወረደው አርሲ ነጌሌ በወረደበት ዓመት ተመልሶ መምጣት ችሏል።
05:00 ላይ በቀጠለው መርሐ ግብር አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ከሞጆ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቆ በመለያ ምቶች አቃቂ ቃሊቲ አሸንፏል። እንደመጀመርያው ጨዋታ ሁሉ በሙከራ ያልታጀበው ጨዋታ ከእረፍት በፊት የተሻሉ የነበሩት ሞጆዎች በ45ኛው ደቂቃ ዘላለም ንጉሴ ባስቆጠረው ድንቅ የቅጣት ምት ጎል መምራት ችለዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ አቃቂዎች በደጋፊዎቻቸው በመታገዝ ሙሉ ብልጫ የወሰዱ ሲሆን ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር በመጨረሻም ተቀይሮ የገባው አብዱልሀሚድ ሰዒድ በ77ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል አቻ ሆነዋል። ጨዋታው በዚሁ ውጤት ተጠናቆ በተሰጡት የመለያ ምቶች በድምሩ 5 ምቶች መክነው አቃቂ ቃሊቲ 4-3 በማሸነፍ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል። በ2009 በወልዲያ የተደረገው የክልል ክለቦች ሻምፒዮናን በበላይነት አጠናቆ ወደ አንደኛ ሊግ ያደገው አቃቂ ቃሊቲ በአንደኛ ሊጉም ከአንድ ዓመት በላይ ሳይቆይ ወደ ከፍተኛ ሊግ አድጓል።
08:00 ላይ ናኖ ሁርቡን ከከንባታ ሺንሺቾ ያገናኘው ጨዋታ በሺንሺቾ አሸናፊነት ተጠናቋል። በበርካታ የሺንሺቾ ደጋፊዎች የደመቀው ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር ተስተናግዶበታል። በ39ኛው ደቂቃ በሺንሺቾ የግብ ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ዓለማየሁ በአግባቡ ተጠቅሞ ናኖ ሁርቡን ቀዳሚ ቢያደርግም ወደ እረፍት ከማምራታቸው በፊት ብርሀኑ ኦርዴላ ወደ ግብ የመታው ኳስ በነኖ ሁርቡው ይልቃል እጅጉ ተጨርፎ አቅጣጫ በመቀየር ወደ ግብነት ተለውጦ ሺንሺቾዎች አቻ መሆን ችለዋል።
ከእረፍት መልስ ሺንሺቾዎች ተሻሽለው በመቅረብ ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል። በ51ኛው ደቂቃ ብርሀኑ ኦርዴላ ከመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ይዞ በመግባት ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሲያመክን በ54ኛው ደቂቃ ከሜዳው የቀኝ ክፍል በግምት ከ25 ሜትር የተገኘውን ቅጣት ምት ኤፍሬም ታመረ በግሩም ሁኔታ በመምታት አስቆጥሮ ሺንሺቾን ወደ መሪነት አሸጋግሮ ጨዋታው በሺንሺቾ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎ እንደ አቃቂ ቃሊቲ ሁሉ ዘንድሮ ወደ አንደኛ ሊጉ የተቀላቀለው ከንባታ ሺንሺቾ ወደ ከፍተኛ ሊጉ በማደግ ታሪክ ሰርቷል።
ከቀደሙት ጨዋታዎች ሁሉ የተለየ የመሸናነፍ ፉክክር የታየበት፣ ተደጋጋሚ የኃይል አጨዋወት የተስተዋለበት እና ከልክ ያለፈ ስሜታዊነት የተንፀባረቀበት በመደበኛው ዙር አንድ ምድብ ላይ የነበሩት ገላን ከተማ እና ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ያገናኘው የእለቱ የመጨረሻ መርሀ ግብር በገላን 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ17 እና 20 ዓመት በታች ውድድሮች ላይ የተመለከትናቸው በርካታ ወጣቶችን የያዙት ሁለቱ ቡድኖች ገና ጨዋታው አንድ ደቂቃ እንዳስቆጠረ የግብ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በ11ኛው ደቂቃ የቢሾፍቱው አሌክሳንደር ዐወት ኳሷን በግብ ጠባቂው ላይ አሳልፎ ቋሚ የገጨበት ሌላዋ ተጠቃሽ ሙከራ ስትሆን በ38ኛው ደቂቃ ማራኪ በሆነ ሒደት ወደ ግብ ክልል የቀረበውን ኳስ አቤል ማርቆስ በምርጥ አጨራረስ አስቆጥሮ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቮችን ቀዳሚ አድርጓል።
ከጎሉ በኋላ በፍጥነት ወደ ጎል መቅረብ የጀመሩት ገላኖች በ1ኛው ደቂቃ የኋላሸት ፍቃዱ ከውስጥ ተከላካዮችን አምልጦ በመውጣት ሞክሮ ግብ ጠባቂ ያወጣበት ኳስ አቻ ልታደርጋቸው የተቃረበች ነበረች። በ45ኛው ደቂቃ ደግሞ በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት አቡበከር ዓሊ አጨራረሱን አሳምሮ ገላንን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከእረፍት በኋላ ጨዋታው ቁጭ ብድግ ማድረጉን ሲቀጥል የማራኪነቱንም ያህል የኃይል አጨዋወት እና ግብግቦች መልኩን ሲያበላሹት ተስተውሏል። ተቀይሮ የገባው የቀድሞው የአካዳሚ ሰልጣኝ እሸቱ ጌታሁን በ57ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ ከተንቀሳቀሰው አንተነህ ደርቤ የተሻገረለትን ኳስ በማስቆጠር ገላንን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር በድጋሚ በ90ኛው ደቂቃ ከመሐመድ ሽክና የተሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት ለውጦ የገላንን መሪነት አስተማማኝ ማድረግ ችሏል።
በተጨማሪው ደቂቃ በቢሾፍተለ አውቶሞተቲቭ ተጫዋች የተመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ወደ ግብ ስታመራ ግብ ጠባቂው ቢያወጣትም የመሐል ዳኛው በጎልነት ማፅደቃቸውን ተከትሎ ውዝግብ አስነስቷል። የገላን ተጫዋቾች ዳኛውን የማዋከብ ተግባር ሲፈፅሙ በሁለቱም በኩል የነበሩ የስታፍ አባላትም የግርግሩ ተሳታፊ ሆነው ታይተዋል። በመጨረሻም ጨዋታውን ገላን በ3-2 አሸናፊነት አጠናቆ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደግ ችሏል።
ወደ ከፍተኛ ሊግ የገቡ አራት ቡድኖች የታወቁበት የማጠቃለያ ውድድር በሳምንቱ መጨረሻ ሲቀጥል የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች እና ዛሬ ሽንፈት ባስተናገዱ ክለቦች መካከል የሚደረጉ ወሳኝ የመለያ ጨዋታዎች ይከናወናሉ። በመለያ ጨዋታዎችም ተጨማሪ ሁለት ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ይሆናል።